የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 50

50
የእስራኤል ኀጢአትና የእግዚአብሔር ባሪያ ታዛዥነት
1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እናታችሁን የፈታሁበት
የፍች ወረቀት የት አለ?
ወይስ እናንተን የሸጥኋችሁ
ለየትኛው አበዳሪዬ ነው?
እነሆ፤ ስለ ኀጢአታችሁ ተሸጣችኋል፤
ስለ መተላለፋችሁም እናታችሁ ተፈትታለች።
2በመጣሁ ጊዜ ለምን በዚያ ሰው አልነበረም?
በተጣራሁስ ጊዜ የሚመልስ ሰው እንዴት በዚያ ታጣ?
ስለ እናንተ ወጆ ለመክፈል ክንዴ ዐጥራ ነበርን?
እናንተንስ ለማዳን ኀይል አነሰኝን?
እነሆ፤ በተግሣጼ ባሕሩን አደርቃለሁ፤
ወንዞችን ምድረ በዳ አደርጋለሁ፤
ዓሦቻቸው ውሃ በማጣት ይሸታሉ፤
በጥማትም ይሞታሉ።
3ሰማይን ጨለማ አለብሰዋለሁ፤
ማቅን መሸፈኛው አደርጋለሁ።”
4ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤
ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤
በየማለዳው ያነቃኛል፤
በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል።
5ልዑል እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶታል፤
እኔም ዐመፀኛ አይደለሁም፤
ወደ ኋላም አላፈገፈግሁም።
6ለሚገርፉኝ ጀርባዬን፣
ጢሜን ለሚነጩ ጕንጬን ሰጠሁ፤
ፊቴን ከውርደት፣
ከጥፋትም አልሰወርሁም።
7ጌታ እግዚአብሔር ስለሚረዳኝ አልዋረድም፤
ስለዚህ ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ
አድርጌአለሁ፤
እንደማላፍርም ዐውቃለሁ።
8የሚያጸድቀኝ በአጠገቤ አለ፤
ታዲያ ማን ሊከስሰኝ ይችላል?
እስኪ ፊት ለፊት እንጋጠም!
ተቃዋሚዬስ ማን ነው?
እስኪ ይምጣ!
9የሚረዳኝ እርሱ ጌታ እግዚአብሔር ነው፤
የሚፈርድብኝስ ማን ነው?
እነሆ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤
ብልም ይበላቸዋል።
10ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣
የባሪያውንም ቃል የሚሰማ ማን ነው?
ያ ሰው በጨለማ የሚሄድ ከሆነና፣
ብርሃንም ከሌለው፣
እግዚአብሔር ስም ይታመን፤
በአምላኩም ይደገፍ።
11አሁን ግን እናንተ እሳት አንድዳችሁ፣
የራሳችሁን የሚንቦገቦግ ችቦ የያዛችሁ ሁሉ፣
በሉ በእሳታችሁ ብርሃን ሂዱ፤
ባንቦገቦጋችሁትም የችቦ ብርሃን ተመላለሱ።
እንግዲህ ከእጄ የምትቀበሉት ይህ ነው፤
በሥቃይም ትጋደማላችሁ።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 50: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ