ኢሳይያስ 61

61
የተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት
1የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤
ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣
እግዚአብሔር ቀብቶኛልና።
ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣
ለምርኮኞች ነጻነትን፣
ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ#61፥1 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን፣ ዕውራንን ከጨለማ አወጣቸው ዘንድ ይላል። ልኮኛል።
2የተወደደችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት፣
የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣
የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤
3በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣
በዐመድ ፈንታ፣
የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣
በልቅሶ ፈንታ፣
የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣
በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣
የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤
እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣
እግዚአብሔር የተከላቸው፣
የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
4የጥንት ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤
በቀድሞ ጊዜ የወደሙትን መልሰው ያቆማሉ፤
ከብዙ ትውልድ በፊት የወደሙትን
ፍርስራሽ ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ።
5መጻተኞች የበግ መንጎቻችሁን ያግዳሉ፤
ባዕዳን በዕርሻችሁና በወይን ተክል ቦታችሁ ላይ ይሠሩላችኋል።
6እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤
የአምላካችን ባሮች ትባላላችሁ፤
የመንግሥታትን ሀብት ትመገባላችሁ፤
በብልጽግናቸውም ትኰራላችሁ።
7ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣
ዕጥፍ ይቀበላሉ፤
በውርደታቸው ፈንታ፣
በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤
የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤
ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።
8“እኔ እግዚአብሔር ፍትሕን ስለምወድድ፣
ዝርፊያንና በደልን እጠላለሁ፤
በታማኝነቴም የሚገባቸውን እሰጣቸዋለሁ፤
ከእነርሱም ጋራ የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።
9ዘሮቻቸው በመንግሥታት፣
ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ የታወቁ ይሆናሉ፤
የሚያዩአቸውም ሁሉ፣
እግዚአብሔር የባረካቸው ሕዝብ እንደ ሆኑ ያውቃሉ።”
10እግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤
ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤
ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣
ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣
የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤
የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
11ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣
የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣
ጌታ እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣
ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 61: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ