የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 13

13
የሳምሶን መወለድ
1እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት እንዲገዙ አሳልፎ ሰጣቸው።
2ማኑሄ የተባለ ከዳን ወገን የተወለደ አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፤ ሚስቱ መካን ስለ ነበረች ልጅ አልወለደችም። 3እግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ አንቺ መካን ነሽ፤ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። 4እንግዲህ ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኩስ ነገርም አትብዪ፤ 5ምክንያቱም ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ልጁ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለአምላክ የተለየ ይሆናልና፤ እስራኤልንም ከፍልስጥኤማውያን እጅ መታደግ ይጀምራል።”
6ከዚያም ሴቲቱ ወደ ባሏ ሄዳ እንዲህ አለችው፤ “የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፤ የእግዚአብሔር መልአክ የሚመስልና እጅግ የሚያስደነግጥ ነበር። ከየት እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፤ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤ 7ነገር ግን፣ ‘ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጪ፤ ርኩስ ነገር አትብዪ፤ ልጁም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና’ ብሎኛል።”
8ከዚያም ማኑሄ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ አንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
9እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሴቲቱ በዕርሻ ውስጥ ሳለች ተገለጠላት፤ በዚህ ጊዜ ግን ባሏ ማኑሄ ዐብሯት አልነበረም። 10እርሷም ለባሏ ለመንገር ፈጥና በመሄድ፣ “ባለፈው ጊዜ የተገለጠልኝ ሰው ዛሬም ተገለጠልኝ” አለችው።
11ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተላት፤ ሰውየው እንደ ደረሰም፣ “ከሚስቴ ጋራ ተነጋግረህ የነበርኸው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም፤ “አዎን እኔ ነኝ” አለው።
12ማኑሄም፣ “ያልኸው በሚፈጸምበት ጊዜ የልጁ ሕይወት የሚመራው እንዴት ነው? እኛስ ምን ማድረግ አለብን?” ሲል ጠየቀው።
13እግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን እንዲህ አለው፤ “ሚስትህ የነገርኋትን ሁሉ ታድርግ። 14ከወይን ተክል የሚገኝ ማንኛውንም ነገር አትብላ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ ርኩስ ነገር አትብላ፤ ያዘዝኋትንም ሁሉ ታድርግ።”
15ከዚያም ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ፣ “የፍየል ጠቦት ዐርደን እስክናዘጋጅልህ ድረስ እባክህ ቈይ” አለው።
16እግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን፣ “የግድ ብታቈየኝ እንኳ የምታቀርበውን ማንኛውንም ምግብ አልበላም፤ ነገር ግን የሚቃጠል መሥዋዕት የምታዘጋጅ ከሆነ እርሱን ለእግዚአብሔር አቅርበው” አለው። የሚያነጋግረው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር።
17ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ፣ “የተናገርኸው ሲፈጸም እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?” በማለት ጠየቀው።
18እግዚአብሔርም መልአክ፣ “ስሜ ድንቅ#13፥18 ወይም ድንቁ ስለ ሆነ፣ ለምን ትጠይቀኛለህ?” አለው። 19ማኑሄም የፍየሉን ጠቦት ከእህል ቍርባኑ ጋራ ወስዶ በዐለት ላይ ለእግዚአብሔር ሠዋው። ማኑሄና ሚስቱ እያዩ እግዚአብሔር አስደናቂ ነገር አደረገ፤ 20ይኸውም የእሳቱ ነበልባል ከመሠዊያው ወደ ሰማይ ሲወጣ፣ የእግዚአብሔር መልአክ በነበልባሉ ውስጥ ዐረገ። ማኑሄና ሚስቱ ይህን ሲመለከቱ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። 21እግዚአብሔርም መልአክ ለማኑሄና ለሚስቱ ዳግመኛ ባለመገለጡ፣ ቀደም ሲል የተገለጠላቸው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ማኑሄ ዐወቀ።
22ማኑሄም ሚስቱን፣ “እግዚአብሔርን ስላየን ያለ ጥርጥር እንሞታለን” አላት።
23ሚስቱ ግን መልሳ እንዲህ አለችው፣ “እግዚአብሔር ሊገድለን ቢፈልግ ኖሮ፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህል ቍርባኑን ከእጃችን ባልተቀበለን፤ ደግሞም ይህን ነገር ሁሉ ባላሳየንና እንዲህ ያለውንም ነገር በዚህ ጊዜ ባልነገረን ነበር።”
24ሴቲቱ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳምሶን ብላ ጠራችው። ልጁ አደገ፤ እግዚአብሔርም ባረከው፤ 25እግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ሳለ ያነቃቃው ጀመር።

Currently Selected:

መሳፍንት 13: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ