ዮሐንስ 19:4-14

ዮሐንስ 19:4-14 NASV

ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ውጭ ወጥቶ፣ “እንግዲህ ወደ እናንተ ያወጣሁት ለክስ የሚያደርስ ወንጀል እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ ነው” አላቸው። ኢየሱስ የእሾኽ አክሊል ደፍቶ ሐምራዊ ልብስም ለብሶ ወጣ፤ ጲላጦስም፣ “እነሆ፤ ሰውየው!” አላቸው። የካህናት አለቆችና አገልጋዮቻቸውም ባዩት ጊዜ፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ ግን፣ “እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት፤ በእኔ በኩል ለክስ የሚያደርስ ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው። አይሁድም፣ “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ። ጲላጦስ ይህን ሲሰማ የባሰውኑ ፈራ፤ ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” በማለት ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። ጲላጦስም፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው። ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው። ከዚያ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ፈለገ፤ አይሁድ ግን፣ “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሳር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሳር ተቃዋሚ ነው” በማለት ጩኸታቸውን ቀጠሉ። ጲላጦስም ይህን ሲሰማ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ “የድንጋይ ንጣፍ” በተባለ፣ በአራማይክ ቋንቋ “ገበታ” ብለው በሚጠሩት ስፍራ፣ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ። ቀኑ የፋሲካ በዓል መዘጋጃ፣ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያህል ነበር። ጲላጦስም አይሁድን፣ “እነሆ፤ ንጉሣችሁ” አላቸው።