ዘሌዋውያን 1

1
የሚቃጠል መሥዋዕት
1 እግዚአብሔር ሙሴን ጠራው፤ ከመገናኛውም ድንኳን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ 2“እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ከእናንተ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር ከእንስሳ ወገን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከላሙ፣ ከበጉ ወይም ከፍየሉ መንጋ መካከል ያቅርብ።
3“ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከላሞች መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ ነቀፋ የሌለበትን ተባዕቱን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያቅርበው። 4የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይም እጁን ይጫን፤ ይህም ያስተሰርይለት ዘንድ በምትኩ ተቀባይነት ያገኛል። 5ወይፈኑን በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን አምጥተው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩት። 6እርሱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም ያውጣው። 7የካህኑ የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ ዕንጨት ረብርበው እሳት ያንድዱበት። 8ካህናቱ የአሮን ልጆች ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምረው ብልቶቹን በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድሩት፤ 9አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም መባውን ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።
10“ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን ያቅርብ። 11የሚቀርበውን መሥዋዕት ከመሠዊያው በስተሰሜን በኩል በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ሁሉ ይርጩት። 12አቅራቢው ብልቶቹን ያውጣ፤ ካህኑም ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምሮ በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድረው፤ 13አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑ መባውን ሁሉ አምጥቶ በመሠዊያው ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።
14“ ‘ለእግዚአብሔር በሚቃጠል መሥዋዕትነት የሚቀርበው መባ ከወፎች ወገን ከሆነ፣ ዋኖስ ወይም የርግብ ጫጩት ያቅርብ። 15ካህኑም ወደ መሠዊያው ያምጣው፤ ራሱን ቈልምሞ ይቀንጥሰው፤ የተቈረጠውንም ራስ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ደሙም በመሠዊያው አጠገብ ይንጠፍጠፍ፤ 16ከሆድ ዕቃውም ጥሬ ቤቱን#1፥16 ለዚህ ቃል የዕብራይስጡ ትርጓሜ በርግጠኛነት አይታወቅም። ለይቶ ከላባዎቹ ጋራ ከመሠዊያው በስተምሥራቅ በኩል፣ ዐመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይጣለው። 17በክንፎቹ በኩል ለሁለት ይሰንጥቀው፤ ነገር ግን ጨርሶ አያለያየው፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ያቃጥለው፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 1: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ