ዘሌዋውያን 12
12
ከወሊድ በኋላ የመንጻት ሥርዐት
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሴት አርግዛ ወንድ ልጅ በምትወልድበት ጊዜ፣ ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን ትረክሳለች። 3ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ሸለፈቱን ይገረዝ። 4ሴትዮዋም ከደሟ እስክትነጻ ድረስ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቈይ፤ የመንጻቷም ወራት እስኪፈጸም ድረስ ማንኛውንም የተቀደሰ ነገር አትንካ፤ ወደ ቤተ መቅደስም አትግባ። 5ነገር ግን የወለደችው ሴት ልጅ ከሆነ፣ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ሁለት ሳምንት ትረክሳለች፤ ከዚያም ከደሟ እስክትነጻ ስድሳ ስድስት ቀን ትቈይ።
6“ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ልጅዋን ወልዳ የመንጻቷ ጊዜ ሲፈጸም፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የአንድ ዓመት ጠቦት፣ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ የዋኖስ ጫጩት ወይም አንድ ርግብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዳ ካህኑ ዘንድ ታቅርብ። 7ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቅርበው፤ ያስተስርይላትም፤ ሴትዮዋም ከደሟ ፈሳሽ ትነጻለች።
“ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ብትወልድ ሕጉ ይኸው ነው። 8ጠቦት ለማምጣት ዐቅሟ ካልፈቀደ፣ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች፣ አንዱ ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ ሌላው ደግሞ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቅርብ፤ በዚህም ካህኑ ያስተሰርይላታል፤ እርሷም ትነጻለች።’ ”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.