ዘሌዋውያን 23

23
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘የተቀደሱ ጉባኤዎች ብላችሁ የምትዋጇቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው።
ሰንበት
3“ ‘ሥራ የምትሠሩበት ስድስት ቀን አላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት፣ የተቀደሰ ጉባኤ ዕለት ነው። የእግዚአብሔር ሰንበት ስለ ሆነ፣ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩበት።
የፋሲካና የቂጣ በዓል
23፥4-8 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20ዘኍ 28፥16-25ዘዳ 16፥1-8
4“ ‘የተመረጡ የእግዚአብሔር በዓላት ብላችሁ በተወሰኑላቸው ጊዜያት የምታውጇቸው የተቀደሱ ጉባኤዎች እነዚህ ናቸው፤ 5የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የእግዚአብሔር ፋሲካ በዓል ይጀመራል። 6በዚያው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ይጀመራል፤ ለሰባት ቀንም ቂጣ ብሉ። 7በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አታከናውኑ። 8ሰባት ቀን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ በዚያ ዕለት የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑ።’ ”
የበኵራት ስጦታ በዓል
9 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 10“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ ከሰበሰባችሁት እህል የመጀመሪያውን ነዶ ለካህኑ አቅርቡ፤ 11ነዶው ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዘው፤ ካህኑ ነዶውን የሚወዘውዘው በሰንበት ቀን ማግስት ነው። 12ነዶውን በምትወዘውዙበት ቀን እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ 13ከዚህም ጋራ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ሁለት ዐሥረኛ የኢፍ#23፥13 4.5 ሊትር ገደማ ይሆናል፤ እንዲሁም 17 ይመ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ለእህል ቍርባን፣ አንድ አራተኛ የሂን#23፥13 1 ሊትር ገደማ ይሆናል መስፈሪያ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን አቅርቡ። 14ስጦታውን ለአምላካችሁ እስከምታቀርቡበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ እንጀራም ቢሆን ቈሎ ወይም እሸት አትብሉ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።
የመከር በዓል
23፥15-22 ተጓ ምብ – ዘኍ 28፥26-31ዘዳ 16፥9-12
15“ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቍጠሩ። 16እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ ዐምሳ ቀን ቍጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቍርባን ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 17በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር አምጡ። 18ከእንጀራውም ጋራ ሰባት ነውር የሌለባቸው የአንድ ዓመት እንከን የሌለው ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ፤ እነዚህም ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋራ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው። 19እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት#23፥19 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል አቅርቡ። 20ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋራ የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው። 21በዚያ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።
22“ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”
የመለከት በዓል
23፥23-25 ተጓ ምብ – ዘኍ 29፥1-6
23 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 24“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በመለከት ድምፅም የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ። 25መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ”
የስርየት ቀን
23፥26-32 ተጓ ምብ – ዘሌ 16፥2-34ዘኍ 29፥7-11
26 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 27“የሰባተኛው ወር ዐሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች ነገርም አትብሉ፤ መሥዋዕትም በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 28እግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ለእናንተ ስርየት የሚደረግበት የስርየት ቀን ስለ ሆነ፣ በዚያ ዕለት ምንም ሥራ አትሥሩ። 29በዚያ ዕለት ሰውነቱን የማያጐሳቍል ማንኛውም ሰው ከወገኖቹ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። 30በዚያ ዕለት ማንኛውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከወገኖቹ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 31ማንኛውንም ሥራ ከቶ አትሥሩበት፤ ይህ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው። 32ይህ ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ስለ ሆነ፣ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ#23፥32 ወይም ጹሙ በወሩም ከዘጠነኛው ቀን ምሽት ጀምራችሁ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ሰንበታችሁን አክብሩ።”
የዳስ በዓል
23፥33-43 ተጓ ምብ – ዘኍ 29፥12-39ዘዳ 16፥13-17
33 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 34“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሰባተኛውም ወር በገባ በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይጀምራል፤ እስከ ሰባት ቀንም ይቈያል። 35የመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነውና የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት። 36ሰባት ቀን መሥዋዕቱን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑበት።
37“ ‘የሚቃጠል መሥዋዕትንና የእህል ቍርባንን፣ መሥዋዕትንና የመጠጥ ቍርባንን በተመደበላቸው ቀን ለእግዚአብሔር በእሳት ለማቅረብ፣ የተቀደሱ ጉባኤዎችን የምታውጁባቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 38እነዚህ መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር ሰንበት ከምታቀርቡት፣ ከስጦታችሁ፣#23፥38 ወይም እነዚህ በዓላት ከእግዚአብሔር ሰንበታት በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ናቸው፤ ስጦታዎቹም ከስእለታችሁና ከበጎ ፈቃድ ስጦታችሁ በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ስጦታዎች ናቸው።
39“ ‘የምድራችሁን ፍሬ ከሰበሰባችሁ በኋላ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ጀምራችሁ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር በዓል አክብሩ፤ የመጀመሪያው ቀን የዕረፍት ዕለት ነው፤ ስምንተኛውም ቀን እንደዚሁ የዕረፍት ዕለት ይሆናል። 40በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ የለመለመ ዛፍ ቅርንጫፍ የአኻያ ዛፍ ቅርንጫፍ ይዛችሁ ሰባት ቀን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 41በየዓመቱም የእግዚአብሔር በዓል አድርጋችሁ ሰባት ቀን አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው፤ በሰባተኛውም ወር አክብሩት። 42ሰባት ቀን ዳስ ውስጥ ተቀመጡ፤ በትውልዱ እስራኤላዊ የሆነ ሁሉ ዳስ ውስጥ ይሰንብት፤ 43በዚህም እኔ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባወጣሁ ጊዜ፣ ዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”
44በዚህ ሁኔታም ሙሴ የተመረጡትን የእግዚአብሔር በዓላት ለእስራኤላውያን አስታወቀ።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 23: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ