ዘሌዋውያን 6

6
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ማንኛውም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ወይም በመያዣነት የተቀበለውን በማጕደልና ባልንጀራውን በማጭበርበር ባይታመን፣ እግዚአብሔርንም ቢበድል ወይም ባልንጀራውን ቢቀማው ወይም ቢያታልለው፣ 3ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ቢል ወይም በሐሰት ቢምል ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ኀጢአት ቢሠራ፣ 4በዚህ ሁኔታ ኀጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣ የሰረቀውን ወይም የቀማውን ወይም በዐደራ የተሰጠውን ወይም ጠፍቶ ያገኘውን ይመልሳል፤ 5በሐሰት የማለበትንም ሁሉ ይመልስ፤ የበደል መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ የወሰደውን በሙሉ የዋናውን አንድ ዐምስተኛ በመጨመር ለባለንብረቱ ንብረቱ ይመልስ። 6ከመንጋውም እንከን የሌለበትን ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ አውራ በግ ስለ በደሉ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ 7በዚህም ሁኔታ ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ስለ ፈጸመው ስለ ማንኛውም በደል ይቅር ይባላል።”
የሚቃጠል መሥዋዕት
8 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 9“አሮንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ስለሚቃጠለው መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጥ፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ሲነድድ ይደር። 10ካህኑም ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ሱሪውን ካጠለቀ በኋላ፣ የበፍታ ቀሚሱን ይልበስ፤ እሳቱ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕቱን ከበላው በኋላ የሚቀረውን ዐመድ አንሥቶ፣ በመሠዊያው አጠገብ ያፍስስ። 11ከዚያም ልብሱን አውልቆ ሌላ ልብስ ይቀይር፤ ዐመዱንም ተሸክሞ ከሰፈር ውጭ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነ ስፍራ ይውሰድ። 12በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምን ጊዜም አይጥፋ። ካህኑ ጧት ጧት እሳቱ ላይ ማገዶ ይጨምር፤ በእሳቱ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያዘጋጅ፤ በዚህም ላይ የኅብረት መሥዋዕቱን#6፥12 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል። ሥብ ያቃጥል። 13በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምን ጊዜም አይጥፋ።
የእህል ቍርባን
14“ ‘የእህል ቍርባን ሥርዐት ይህ ነው፦ የአሮን ልጆች ቍርባኑን በመሠዊያው ትይዩ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርቡት። 15ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ያንሣለት፤ በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውንም ዕጣን በሙሉ ይውሰድ፤ ይህንም፣ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ፣ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። 16የተረፈውንም አሮንና ልጆቹ ይብሉት፤ ቂጣውን በተቀደሰው ስፍራ፣ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ አደባባዩ ላይ ይብሉት። 17ያለ እርሾ መጋገር አለበት፤ በእሳት ከሚቀርብልኝ ቍርባን ይህን የእነርሱ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም፣ እንደ ኀጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ነው። 18ማንኛውም ከአሮን ዘር የተወለደ ወንድ ሊበላው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የእሳት ቍርባን ለርሱ የተመደበ የዘላለም ድርሻው ነው፤ የሚነካውም ሁሉ#6፥18 ወይም የሚነካው ሰው ሁሉ፤ እንዲሁም 27 ይመ ቅዱስ ይሆናል።’ ”
19 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 20“አሮን ወይም ልጆቹ በተቀቡበት ዕለት#6፥20 ወይም በተቀባበት ዕለት አሮን እና ልጆቹእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፦ የኢፍ#6፥20 1.6 ኪሎ ግራም ይሆናል። አንድ ዐሥረኛው የላመ ዱቄት ግማሹን ለጧት፣ ግማሹን ለማታ የዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ያቅርቡት። 21በሚገባ በዘይት ተለውሶ በምጣድ ላይ ይጋገር፤ ከዚያም የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ#6፥21 የዚህ ቃል የዕብራይስጡ ትርጓሜ በርግጠኛነት አይታወቅም ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ አቅርብ። 22በርሱ ቦታ ተቀብቶ ካህን የሚሆነው ልጁ ይህን ያዘጋጅ፤ ለእግዚአብሔር የተመደበ ድርሻ ነውና ፈጽሞ ይቃጠል። 23ካህኑ የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠል እንጂ አይበላ።”
የኀጢአት መሥዋዕት
24 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 25“አሮንንና ልጆቹን እንዲህ በላቸው፤ ‘ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኀጢአቱም መሥዋዕት እዚያው በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው። 26መሥዋዕቱንም የሚያቀርበው ካህን ይብላው፤ ይህም በተቀደሰው ስፍራ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ በአደባባዩ ላይ ይበላ። 27ሥጋውን የሚነካ ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ ደሙ በልብስ ላይ ቢረጭ፣ ያን ልብስ በተቀደሰ ስፍራ ዕጠብ። 28ሥጋው የተቀቀለበት የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ የናስ ዕቃ ከሆነ ግን ተፈግፍጎ በውሃ ይታጠብ። 29ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው። 30ነገር ግን ደሙ ማስተስረያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን ወደ ቅድስት የቀረበው የኀጢአት መሥዋዕት ሁሉ በእሳት ይቃጠል እንጂ አይበላ።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 6: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ