የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 20

20
የኢየሱስ ሥልጣን ለአይሁድ አጠያያቂ ሆነባቸው
20፥1-8 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥23-27ማር 11፥27-33
1አንድ ቀን ኢየሱስ ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምርና ወንጌልን ሲሰብክ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ። 2እነርሱም፣ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን እንደ ሆነ ንገረን፤ ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።
3እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ እስኪ መልሱልኝ፤ 4የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰው?”
5እነርሱም እንዲህ ብለው እርስ በርስ ተመካከሩ፤ “ ‘ከሰማይ’ ብንል፣ ‘ታዲያ፣ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ 6‘ከሰው’ ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ መሆኑን ስለሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።”
7ስለዚህ፣ “ከየት እንደ ሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት።
8ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።
የጭሰኞቹ ምሳሌ
20፥9-19 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥33-46ማር 12፥1-12
9ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎችም አከራየና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ብዙ ጊዜ ቈየ። 10በመከርም ወራት፣ ከወይኑ ፍሬ እንዲልኩለት ባሪያውን ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ባሪያውን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት። 11ቀጥሎም ሌላ ባሪያውን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት። 12አሁንም ቀጥሎ ሦስተኛ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ አቍስለው ወደ ውጭ ጣሉት።
13 “የወይኑ ተክል ባለቤትም፣ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? እስኪ ደግሞ የምወድደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል’ አለ።
14 “ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህ እኮ ወራሹ ነው፣ ኑና እንግደለው፤ በዚህም ርስቱ የእኛ ይሆናል’ እየተባባሉ ተመካከሩ፤ 15ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት።
“እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል? 16መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።”
ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ።
17ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤
“ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣
እርሱ የማእዘን ራስ # 20፥17 ወይም የማእዘን ድንጋይ ሆነ’#20፥17 መዝ 118፥22 ተብሎ የተጻፈው ትርጕሙ ምንድን ነው?
18 በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቅቃል።”
19ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ።
ለቄሳር ግብር መክፈል
20፥20-26 ተጓ ምብ – ማቴ 22፥15-22ማር 12፥13-17
20ኢየሱስን አሳልፈው ለገዢው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት። 21ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን። 22ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”
23እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ 24“እስኪ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?”
እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት።
25እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።
26ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።
ትንሣኤ ሙታንና ጋብቻ
20፥27-40 ተጓ ምብ – ማቴ 22፥23-33ማር 12፥18-27
27ትንሣኤ የለም ከሚሉት ሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ወደ ኢየሱስ መጥተው ጥያቄ አቀረቡለት፤ 28እንዲህም አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ የሟችን ሚስት አግብቶ ልጆች በመውለድ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። 29ታዲያ፣ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ 30ሁለተኛውም እንደዚሁ፤ 31ሦስተኛው ደግሞ አገባት፤ ሰባቱም እንዲሁ እያሉ አግብተዋት ልጆች ሳይወልዱ ሞቱ። 32በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች። 33እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት፣ በትንሣኤ ጊዜ የማን ሚስት ትሆናለች?”
34ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ፤ ይጋባሉም፤ 35የሚመጣውን ዓለምና የሙታንን ትንሣኤ ማግኘት የሚገባቸው ግን አያገቡም፤ አይጋቡም፤ 36እንደ መላእክትም ስለሚሆኑ ከዚያ በኋላ አይሞቱም፤ የትንሣኤ ልጆች ስለ ሆኑም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። 37ሙሴ ስለ ቍጥቋጦ በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ጌታን፣ ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ’#20፥37 ዘፀ 3፥6 በማለቱ ሙታን እንደሚነሡ ያሳያል፤ 38ሁሉም ለርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፣ እርሱ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አይደለም።”
39አንዳንድ ጸሐፍትም፣ “መምህር ሆይ፤ መልካም ተናገርህ” አሉት። 40ከዚህ በኋላ አንድ ሰው እንኳ ሊጠይቀው አልደፈረም።
ክርስቶስ የማን ልጅ ነው?
20፥41-47 ተጓ ምብ – ማቴ 22፥41–23፥7ማር 12፥35-40
41ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ክርስቶስን#20፥41 ወይም መሲሕ እንዴት የዳዊት ልጅ ነው ይሉታል? 42ምክንያቱም ራሱ ዳዊት በመዝሙር መጽሐፉ እንዲህ ብሏል፤
“ ‘ጌታ ጌታዬን፣
“በቀኜ ተቀመጥ፤
43 ጠላቶችህን፣
ለእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ።” ’ # 20፥43 መዝ 110፥1
44 እንግዲህ ዳዊት እርሱን፣ ‘ጌታ’ ብሎ ሲጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”
45ሕዝቡ ሁሉ እየሰሙትም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፤ 46ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ “ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሰው መዞርን፣ በገበያ ስፍራ የአክብሮት ሰላምታን፣ በምኵራብ የከበሬታ መቀመጫን፣ በግብዣ ቦታም የክብር ስፍራን ይፈልጋሉና፤ 47በረዥም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቍታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።”

Currently Selected:

ሉቃስ 20: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ