የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 3

3
የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት
3፥2-10 ተጓ ምብ – ማቴ 3፥1-10ማር 1፥3-5
3፥16-17 ተጓ ምብ – ማቴ 3፥11-12ማር 1፥7-8
1ጢባርዮስ ቄሳር በነገሠ በዐሥራ ዐምስተኛው ዓመት፣ ይኸውም ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ሊሳኒዮስም የሳቢላኒስ አራተኛው ክፍል ገዥ በነበሩበት ጊዜ፣ 2ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። 3እርሱም ለኀጢአት ስርየት የሚሆን የንስሓን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ወዳሉት ስፍራዎች ሁሉ መጣ፤ 4ይኸውም፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል በጻፈው ቃል መሠረት ነበር፤
“በምድረ በዳ እንዲህ ብሎ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤
‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤
ጐዳናውንም አቅኑ፤
5ሸለቆው ሁሉ ይሞላል፤
ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤
ጠማማው መንገድ ቀና፣
ወጣ ገባውም ጐዳና ለጥ ያለ ሜዳ ይሆናል፤
6የሰውም ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያል።’ ”#3፥6 ኢሳ 40፥3-5
7ዮሐንስም በርሱ እጅ ሊጠመቁ የወጡትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የእፉኝት ልጆች! ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ? 8እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ደግሞም በልባችሁ፣ ‘አብርሃም አባት አለን’ ማለትን አትጀምሩ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና። 9እነሆ፤ ምሣር የዛፎችን ሥር ሊቈርጥ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል።”
10ሕዝቡም፣ “ታዲያ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።
11ዮሐንስም፣ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ” ብሎ መለሰላቸው።
12ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው፣ “መምህር ሆይ፤ እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት።
13እርሱም፣ “ከታዘዛችሁት በላይ ቀረጥ አትሰብስቡ” አላቸው።
14ወታደሮች ደግሞ፣ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።
እርሱም፣ “የማንንም ገንዘብ በግፍ አትንጠቁ፤ ሰውንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁ ይብቃችሁ” አላቸው።
15ሕዝቡ በጕጕት እየተጠባበቁ ሳሉ፣ “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ ያሰላስሉ ነበር። 16ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታው ይመጣል፤ እኔም የጫማውን ማሰሪያ መፍታት የሚገባኝ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ 17ዐውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውንም ወደ ጐተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” 18ዮሐንስም በብዙ ሌሎች የምክር ቃላት ሕዝቡን እያስጠነቀቀ ወንጌልን ሰበከላቸው።
19ነገር ግን ዮሐንስ፣ የአራተኛውን ክፍል ገዥ ሄሮድስን የወንድሙ ሚስት በነበረችው በሄሮድያዳ ምክንያትና ስለ ሌሎች ሥራዎቹ በገሠጸው ጊዜ፣ 20ሄሮድስ ይህን በሌላው ሁሉ ላይ በመጨመር፣ ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገባው።
የኢየሱስ መጠመቅና የትውልድ ሐረጉ
3፥21-22 ተጓ ምብ – ማቴ 3፥13-17ማር 1፥9-11
3፥23-38 ተጓ ምብ – ማቴ 1፥1-17
21ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቀ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እየጸለየም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ 22መንፈስ ቅዱስም በአካላዊ ቅርጽ እንደ ርግብ በርሱ ላይ ወረደ፤ ከሰማይም፣ “የምወድድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ መጣ።
23ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ነበር፤ ሕዝቡም እንደ መሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፦
የኤሊ ልጅ፣ 24የማቲ ልጅ፣
የሌዊ ልጅ፣ የሚልኪ ልጅ፣
የዮና ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣
25የማታትዩ ልጅ፣ የአሞጽ ልጅ፣
የናሆም ልጅ፣ የኤሲሊም ልጅ፣
የናጌ ልጅ፣ 26የማአት ልጅ፣
የማታትዩ ልጅ፣ የሴሜይ ልጅ፣
የዮሴፍ ልጅ፣ የዮዳ ልጅ፣
27የዮናን ልጅ፣ የሬስ ልጅ፣
የዘሩባቤል ልጅ፣ የሰላትያል ልጅ፣
የኔሪ ልጅ፣ 28የሚልኪ ልጅ፣
የሐዲ ልጅ፣ የዮሳስ ልጅ፣ የቆሳም ልጅ፣
የኤልሞዳም ልጅ፣ የኤር ልጅ፣
29የዮሴዕ ልጅ፣ የኤልዓዘር ልጅ፣
የዮራም ልጅ፣ የማጣት ልጅ፣
የሌዊ ልጅ፣ 30የስምዖን ልጅ፣
የይሁዳ ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣
የዮናም ልጅ፣ የኤልያቄም ልጅ፣
31የሜልያ ልጅ፣ የማይናን ልጅ፣
የማጣት ልጅ፣ የናታን ልጅ፣
የዳዊት ልጅ፣ 32የእሴይ ልጅ፣
የኢዮቤድ ልጅ፣ የቦዔዝ ልጅ፣
የሰልሞን#3፥32 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ሳላ ይላሉ። ልጅ፣ የነአሶን ልጅ፣
33የአሚናዳብ ልጅ፣ የአራም#3፥33 አንዳንድ ቅጆች የአሚናዳብ ልጅ የአዲም ልጅ የአርኒ ልጅ ይላሉ። ልጅ፣
የአሮኒ ልጅ፣ የኤስሮም ልጅ፣ የፋሬስ ልጅ፣
የይሁዳ ልጅ፣ 34የያዕቆብ ልጅ፣
የይሥሐቅ ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ፣
የታራ ልጅ፣ የናኮር ልጅ፣
35የሴሮህ ልጅ፣ የራጋው ልጅ፣
የፋሌቅ ልጅ፣ የአቤር ልጅ፣
የሳላ ልጅ፣ 36የቃይንም ልጅ፣
የአርፋክስድ ልጅ፣ የሴም ልጅ፣
የኖኅ ልጅ፣ የላሜህ ልጅ፣
37የማቱሳላ ልጅ፣ የሔኖክ ልጅ፣
የያሬድ ልጅ፣ የመላልኤል ልጅ፣
የቃይናን ልጅ፣ 38የሄኖስ ልጅ፣
የሤት ልጅ፣ የአዳም ልጅ፣
የእግዚአብሔር ልጅ።

Currently Selected:

ሉቃስ 3: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ