ማቴዎስ 2
2
የጠቢባን ከምሥራቅ መምጣት
1በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን፣ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ይሁዳ ከተወለደ በኋላ፣ ጠቢባን ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ 2“የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ#2፥2 ወይም ኮከቡ ሲነሣ አይተን ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” ሲሉ ጠየቁ።
3ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላዪቱ ኢየሩሳሌም ዐብራ ታወከች። 4እርሱም የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንን በሙሉ ሰብስቦ፣ ክርስቶስ#2፥4 ወይም መሲሕ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። 5እነርሱም፣ “በይሁዳ ቤተ ልሔም፤ ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፏልና አሉ፤
6“ ‘በይሁዳ ምድር የምትገኚው አንቺ ቤተ ልሔም፣
ከሌሎቹ ከይሁዳ ገዦች በምንም አታንሺም፤
የሕዝቤ የእስራኤል ጠባቂ የሚሆን፣
ከአንቺ ይወጣልና።’ ”#2፥6 ሚክ 5፥2-4
7ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። 8ጠቢባኑንም ወደ ቤተ ልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው።
9ጠቢባኑ ንጉሡ ያለውን ከሰሙ በኋላ ጕዟቸውን ቀጠሉ። ይህም በምሥራቅ#2፥9 ወይም ሲነሣ አይተው ያዩት ኮከብ እየመራቸው ሕፃኑ እስካለበት ድረስ ወሰዳቸው። 10ኮከቡንም ሲያዩ ከመጠን በላይ ተደሰቱ። 11ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋራ አዩ፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት። 12እግዚአብሔርም ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ወደ ግብጽ ሽሽት
13ጠቢባኑ ከሄዱ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሥ! የምትመለስበትን ጊዜ እስካስታውቅህ ድረስ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ በመሸሽ በዚያ ቈይ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻልና” አለው።
14ስለዚህም ዮሴፍ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤ 15በዚያም ሄሮድስ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ኖረ። በዚህም፣ “ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት”#2፥15 ሆሴ 11፥1 በማለት ጌታ በነቢዩ አንደበት የተናገረው ቃል ተፈጸመ።
16ሄሮድስ ጠቢባኑ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ በጣም ተናደደ። ከጠቢባኑ በተነገረው መሠረት፣ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን የቤተ ልሔምንና የአካባቢዋን መንደሮች ወንድ ልጆች ሁሉ ልኮ አስገደለ። 17በዚህም በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤
18“የልቅሶና የታላቅ ዋይታ ድምፅ
በራማ ተሰማ፤
ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤
መጽናናትም እንቢ አለች፤
ልጆቿ ዐልቀዋልና።”#2፥18 ኤር 31፥15
ከግብጽ ወደ ናዝሬት
19ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ 20“ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው።
21ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ 22ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ 23ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ#2፥23 በዘኍልቍ ምዕራፍ 6 ላይ ካለው “ናዝራዊ” ይለያል። ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.