ማርቆስ 1
1
የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት
1፥2-8 ተጓ ምብ – ማቴ 3፥1-11፤ ሉቃ 3፥2-16
1የእግዚአብሔር ልጅ#1፥1 አንዳንድ ቅጆች የእግዚአብሔር ልጅ የሚለው ሐረግ የላቸውም።፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።
2በነቢዩ በኢሳይያስ፣ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤
“እነሆ፤ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን
በፊትህ እልካለሁ፤”
3“የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤
‘ጥርጊያውንም አስተካክሉ’
እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ።”
4ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሓ እያጠመቀና ለኀጢአት ስርየት የንስሓ ጥምቀት እየሰበከ መጣ። 5በመላው ይሁዳ፣ የኢየሩሳሌም ሰዎችም በጠቅላላ ወደ እርሱ በመሄድ ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በርሱ እጅ ተጠመቁ። 6ዮሐንስ የግመል ጠጕር ይለብስ፣ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ፣ አንበጣና የበረሓ ማርም ይበላ ነበር። 7ስብከቱም፣ “እኔ ጐንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት ከማይገባኝ፣ ከእኔ የሚበረታው ከእኔ በኋላ ይመጣል። 8እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” የሚል ነበር።
የኢየሱስ መጠመቅና መፈተን
1፥9-11 ተጓ ምብ – ማቴ 3፥13-17፤ ሉቃ 3፥21-22
1፥12-13 ተጓ ምብ – ማቴ 4፥1-11፤ ሉቃ 4፥1-13
9በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የገሊላ ከተማ ከሆነችው ከናዝሬት መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። 10ከውሃው በሚወጣበትም ጊዜ፣ ሰማያት ተከፍተው፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በርሱ ላይ ሲወርድ አየ፤ 11“የምወድድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።
12ወዲያውም መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድረ በዳ መራው፤ 13በሰይጣንም እየተፈተነ አርባ ቀን በምድረ በዳ ቈየ። ከአራዊት ጋራ ነበር፤ መላእክትም አገለገሉት።
የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መመረጥ
1፥16-20 ተጓ ምብ – ማቴ 4፥18-22፤ ሉቃ 5፥2-11፤ ዮሐ 1፥35-42
14ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ ሄዶ፣ 15“ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ!” እያለ ይሰብክ ነበር።
16ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፣ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። 17ኢየሱስም፣ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። 18እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት።
19ትንሽ ዕልፍ እንዳለ፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፣ 20ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም አባታቸውን በጀልባው ላይ ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋራ ትተው ተከተሉት።
ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ አስወጣ
1፥21-28 ተጓ ምብ – ሉቃ 4፥31-37
21ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። 22እንደ ጸሐፍት ሳይሆን፣ እንደ ባለሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። 23በዚያ ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ#1፥23 ወይም ክፉ፤ እንዲሁም 26 እና 27 ይመ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ 24“የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!”
25ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። 26ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኀይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ከርሱ ወጣ።
27ሁሉም በመገረም፣ “ይህ ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት ምንድን ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል!” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። 28ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ወጣ።
ኢየሱስ ብዙዎችን ፈወሰ
1፥29-31 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥14-15፤ ሉቃ 4፥38-39
1፥32-34 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥16-17፤ ሉቃ 4፥40-41
29ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋራ ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ። 30የስምዖን ዐማት በትኵሳት በሽታ ታምማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤ 31ስለዚህም እርሱ ወደ ተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሣት፤ ትኵሳቱም ተዋት፤ ተነሥታም ታገለግላቸው ጀመር።
32ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፣ ምሽት ላይ የአካባቢው ሰዎች ሕመምተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ። 33የከተማዋ ሕዝብ በሙሉ በቤቱ ደጅ ላይ ተሰብስቦ ነበር። 34እርሱም በተለያየ በሽታ የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትም አወጣ፤ ነገር ግን አጋንንቱ የኢየሱስን ማንነት ያውቁ ስለ ነበር እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።
ኢየሱስ በገለልተኛ ስፍራ ጸለየ
1፥35-38 ተጓ ምብ – ሉቃ 4፥42-43
35ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድድ፣ ኢየሱስ ተነሥቶ ከቤት ወጣ፤ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ ይጸልይ ጀመር። 36ስምዖንና ባልደረቦቹም ተከትለው ይፈልጉት ነበር፤ 37ባገኙትም ጊዜ፣ “ሰው ሁሉ ይፈልግሃል!” አሉት።
38እርሱም፣ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው። 39ስለዚህ በምኵራቦቻቸው እየሰበከና አጋንንትን በማስወጣት በመላዋ ገሊላ ይዘዋወር ጀመር።
ኢየሱስ ለምጻሙን ሰው አነጻ
1፥40-44 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥2-4፤ ሉቃ 5፥12-14
40አንድ ለምጻም#1፥40 ለምጽ የሚለው ቃል በግሪኩ አገላለጽ የተለያዩ የቈዳ በሽታዎችን ያመለክታል። ወደ እርሱ ቀርቦ ከፊቱ በመንበርከክ፣ “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለመነው።
41ኢየሱስም ለሰውየው በመራራት እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፣ ንጻ!” አለው። 42እርሱም ወዲያው ከለምጹ ነጻ፤ ከበሽታውም ተፈወሰ።
43ኢየሱስም ሰውየውን አጥብቆ በማስጠንቀቅ እንዲህ ሲል አሰናበተው፤ 44“ለማንም አንድ ነገር እንኳ እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ምስክር እንዲሆናቸው ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ስለ መንጻትህም ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” አለው። 45ሰውየው ግን በሄደበት ሁሉ ነገሩን በሰፊው አወራ፤ ወሬውንም አሠራጨ። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ወደ ማንኛውም ከተማ በግልጽ መግባት አልተቻለውም፤ ከዚህም የተነሣ ከከተማ ውጭ በሚገኙ ምድረ በዳዎች መኖር ጀመረ፤ ሰዎች ግን ከየአቅጣጫው እርሱ ወዳለበት መምጣት አላቋረጡም።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.