ማርቆስ 4
4
የዘሪው ምሳሌ
4፥1-12 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥1-15፤ ሉቃ 8፥4-10
4፥13-20 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥18-23፤ ሉቃ 8፥1-15
1በሌላ ጊዜ ደግሞ በባሕሩ አጠገብ ያስተምር ጀመር። እርሱ ባለበት አካባቢ እጅግ ብዙ ሕዝብ ስለ ተሰበሰበ፣ በባሕሩ ላይ ወዳለች ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ባለው ስፍራ ላይ ተሰብስቦ ነበር። 2እርሱም ብዙ ነገሮችን በምሳሌ አስተማራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ 3“ስሙ፤ አንድ ዘሪ ዘር ሊዘራ ወጣ። 4ሲዘራም ሳለ አንዳንዱ ዘር መንገድ ላይ ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። 5አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ 6ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። 7ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አድጎ የዘሩን ተክል ስላነቀው ፍሬ አላፈራም። 8ሌላውም ዘር ደግሞ በመልካም መሬት ላይ ስለ ወደቀ በቅሎ አደገ፤ ፍሬም ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፣ አንዱ ስድሳ፣ ሌላውም መቶ ፍሬ አፈራ።”
9ቀጥሎም ኢየሱስ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።
10ብቻውን በሆነ ጊዜ፣ ዐሥራ ሁለቱና ዐብረውት የነበሩት ሌሎች ስለ ምሳሌዎቹ ጠየቁት። 11እርሱም፣ “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ነገር ሁሉ በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ 12ይኸውም፣
“ ‘ማየቱን እንዲያዩ እንዳያስተውሉትም፣
መስማቱን እንዲሰሙ
ልብ እንዳይሉትም፣ እንዳይመለሱና ኀጢአታቸው
እንዳይሰረይላቸው ነው’ አላቸው።”
13ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ምሳሌ አልተረዳችሁትምን? ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? 14ዘሪው ቃሉን ይዘራል። 15አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ላይ የወደቀውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል። 16እንዲሁም ሌሎች በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ 17ነገር ግን ሥር ስላልሰደዱ፣ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። 18ሌሎቹ ደግሞ በእሾኽ መካከል የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን መስማት ይሰማሉ፤ 19ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን ዐንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል። 20ሌሎቹ በመልካም መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ እነዚህም ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”
የመቅረዙ መብራት ምሳሌ
21እንዲህም አላቸው፤ “መብራት ተወስዶ ከእንቅብ በታች ወይም ከዐልጋ ሥር ይቀመጣልን? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለምን? 22ስለዚህ ተደብቆ የማይገለጥ፣ ተሸሽጎ ወደ ብርሃን የማይወጣ የለም፤ 23ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።”
24በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። 25ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው።
የአዳጊው ዘር ምሳሌ
26ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። 27ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ 28ምድርም ራሷ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ 29ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ ዐጨዳ ይጀምራል።”
የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ
4፥30-32 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥31-32፤ ሉቃ 13፥18-19
30ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋራ እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? 31በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ 32ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትልልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።”
33ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው። 34ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ
4፥35-41 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥18፤ 8፥23-27፤ ሉቃ 8፥22-25
35ያ ቀን በመሸ ጊዜ፣ “ወደ ማዶ እንሻገር” አላቸው። 36እነርሱ ሕዝቡን ትተው በጀልባዋ ውስጥ እንዳለ በዚያው ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም ዐብረውት ነበሩ። 37በዚህ ጊዜ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ውሃ እስኪሞላት ድረስ ጀልባዋን ያናውጣት ነበር። 38ኢየሱስ ግን ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። እነርሱም ቀስቅሰውት፣ “መምህር ሆይ፤ ስንጠፋ አይገድድህምን?” አሉት።
39እርሱም ተነሥቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ “ጸጥ፣ ረጭ በል!” አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ ረጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ።
40ደቀ መዛሙርቱንም፣ “ስለ ምን እንዲህ ፈራችሁ? እስከዚህ እምነት የላችሁምን?” አላቸው።
41እነርሱም በፍርሀት ተውጠው እርስ በርሳቸው፣ “ነፋሱም ሞገዱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.