የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍልቍ 20

20
ከዐለት የፈለቀ ውሃ
1በመጀመሪያው ወር መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ወደ ጺን ምድረ በዳ መጥተው በቃዴስ ተቀመጡ፤ እዚያ ማርያም ሞተች፤ ተቀበረችም።
2በዚህ ጊዜ ለማኅበረ ሰቡ የሚሆን ውሃ አልነበረም፤ ሕዝቡም ሙሴንና አሮንን በመቃወም ተሰበሰቡ። 3ሙሴን ተጣሉት፤ እንዲህም አሉት፤ “ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ ምነው እኛም ያኔ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! 4እግዚአብሔርን ማኅበረ ሰብ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድን ነው! ከነከብቶቻችን እዚሁ እንድናልቅ ነውን? 5ከግብጽ አውጥታችሁ እህል ወይም በለስ፣ ወይን ወይም ሮማን ወደሌለበት ወደዚህ ክፉ ቦታ ያመጣችሁንስ ለምንድን ነው? የሚጠጣ ውሃ እንኳ ይታጣ!”
6ሙሴና አሮን ከማኅበረ ሰቡ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው በግንባራቸው ተደፉ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው። 7እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 8“በትሪቱን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን በአንድነት ሰብስቡ፤ እነርሱም እያዩ ዐለቱን ተናገሩት፤ ዐለቱም ውሃ ያወጣል። አንተም ለማኅበረ ሰቡ ከዐለቱ ውሃ ታወጣላቸዋለህ፤ እነርሱና ከብቶቻቸውም ይጠጣሉ።”
9ስለዚህም ሙሴ ልክ እንደ ታዘዘው በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ። 10እርሱና አሮንም ማኅበሩን በዐለቱ ፊት አንድ ላይ ሰበሰቡ፤ ሙሴም፣ “እናንተ ዐመፀኞች ስሙ፤ ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” አላቸው። 11ከዚያም ሙሴ እጁን ዘርግቶ በበትሩ ዐለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ውሃውም ተንዶለዶለ፤ ማኅበረ ሰቡና ከብቶቻቸውም ጠጡ።
12ነገር ግን እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን፣ “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ስላልታመናችሁብኝ ይህን ማኅበረ ሰብ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም” አላቸው።
13እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋራ የተጣሉበት፣ እርሱም ቅዱስ መሆኑን በመካከላቸው የገለጠበት ይህ የመሪባ#20፥13 መሪባ ማለት መጣላት ማለት ነው። ውሃ ነበር።
ኤዶም እስራኤል እንዳያልፍ ከለከለ
14ሙሴ ከቃዴስ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ሲል መልእክተኞች ላከ፤
“ወንድምህ እስራኤል የሚለው ይህ ነው፤ የደረሰብን መከራ ሁሉ ምን እንደ ሆነ አንተም ታውቃለህ። 15የቀድሞ አባቶቻችን ወደ ግብጽ ወረዱ፤ እኛም እዚያ ብዙ ዘመን ኖርን። ግብጻውያን እኛንም አባቶቻችንንም አሠቃዩን፤ 16ወደ እግዚአብሔር በጮኽን ጊዜ ግን ጩኸታችንን ሰማ፤ መልአክ ልኮም ከግብጽ አወጣን።
“አሁንም ያለነው እዚሁ ቃዴስ በግዛትህ ድንበር ላይ ባለችው ከተማ ነው። 17ስለዚህ በአገርህ እንድናልፍ እባክህን ፍቀድልን፤ በየትኛውም ዕርሻ ወይም የወይን ተክል ውስጥ አንገባም፤ ከየትኛውም ጕድጓድ ውሃ አንጠጣም። የንጉሡን አውራ ጐዳና ይዘን ከመጓዝ በቀር፣ ግዛትህን ዐልፈን እስክንሄድ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።”
18ኤዶም ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤
“በዚህ በኩል አታልፉም፤ እናልፋለን የምትሉ ከሆነ በሰልፍ ወጥተን በሰይፍ እንመታችኋለን።”
19እስራኤላውያንም መልሰው፣
“አውራውን መንገድ ይዘን እንሄዳለን፤ እኛም ሆንን ከብቶቻችን የትኛውንም ውሃችሁን ከጠጣን ዋጋውን እንከፍላለን፤ በእግር ዐልፈን መሄድ ብቻ እንጂ ሌላ ምንም አንፈልግም።” አሏቸው።
20ኤዶምም እንደ ገና፣
“በዚህ ማለፍ አትችሉም” የሚል መልስ ሰጣቸው።
ከዚያም ኤዶም ብዙና ኀይለኛ የሆነ ሰራዊት አሰልፎ ሊወጋቸው ወጣ፤ 21ስለዚህ ኤዶም በግዛቱ ዐልፈው እንዳይሄዱ ስለ ከለከላቸው እስራኤላውያን ተመለሱ።
የአሮን መሞት
22መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ከቃዴስ ተነሥቶ ወደ ሖር ተራራ መጣ። 23እግዚአብሔርም በኤዶም ወሰን አጠገብ ባለው በሖር ተራራ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 24“አሮን ወደ ወገኖቹ ይሰበሰባል፤ ሁለታችሁም በመሪባ ውሃ በትእዛዜ ላይ ዐምፃችኋልና ለእስራኤላውያን ወደምሰጣት ምድር አይገባም። 25አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ወደ ሖር ተራራ ይዘሃቸው ውጣ። 26አሮን ወደ ወገኖቹ ስለሚሰበሰብ ልብሱን አውልቀህ ልጁን አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም እዚያው ይሞታል።”
27ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ መላው ማኅበረ ሰብ እያያቸው ወደ ሖር ተራራ ወጡ። 28ሙሴም የአሮንን ልብስ አውልቆ ልጁን አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም እዚያው ተራራው ጫፍ ላይ ሞተ። ከዚያም ሙሴና አልዓዛር ከተራራው ወረዱ፤ 29መላው ማኅበረ ሰብም አሮን መሞቱን በተረዳ ጊዜ፣ የእስራኤል ቤት በሙሉ ሠላሳ ቀን አለቀሰለት።

Currently Selected:

ዘኍልቍ 20: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ