የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍልቍ 8

8
የመብራቶቹ አቀማመጥ
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“አሮንን ተናገረው፤ እንዲህም በለው፤ ‘ሰባቱን መብራቶች በየቦታቸው በምታስቀምጥበት ጊዜ በመቅረዙ ፊት ለፊት ላለው አካባቢ ብርሃን ይሰጣሉ።’ ”
3አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት መብራቶቹ በመቅረዙ ላይ ሆነው ፊት ለፊት እንዲያበሩ አስቀመጣቸው። 4የመቅረዙ አሠራር እንዲህ ነበር፤ ከመቆሚያው እስከ አበቦቹ ያለው ከተቀጠቀጠ ወርቅ የተሠራ ሲሆን፣ የመቅረዙም አሠራር እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው መሠረት ነበር።
የሌዋውያን ለአገልግሎት መለየት
5 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6“ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ለይተህ በሥርዐቱ መሠረት አንጻቸው። 7ስታነጻቸውም እንዲህ አድርግ፤ በሚያነጻ ውሃ እርጫቸው፤ ገላቸውን በሙሉ በምላጭ ተላጭተው ልብሳቸውን ይጠቡ፤ በዚህም ይንጹ። 8በዘይት ከተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን ጋራ አንድ ወይፈን ይውሰዱ፤ ከዚያም ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን ሌላ ወይፈን አንተ ትወስዳለህ። 9ሌዋውያኑን ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አምጣ፤ መላውንም የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሰብስብ፤ 10ሌዋውያኑን በእግዚአብሔር ፊት አቅርብ፤ ከዚያም እስራኤላውያን እጃቸውን ይጫኑባቸው። 11ከዚያም አሮን ሌዋውያኑን የእግዚአብሔርን አገልግሎት ለማከናወን ዝግጁ እንዲሆኑ ከእስራኤላውያን መካከል እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ያቅርባቸው።
12“ሌዋውያኑ እጃቸውን በወይፈኖቹ ራስ ላይ ከጫኑ በኋላ ለሌዋውያኑ ማስተስረያ ይሆኑ ዘንድ የኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር አቅርባቸው። 13ከዚያም ሌዋውያኑን በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህም ለእግዚአብሔር አቅርባቸው። 14በዚህ መሠረት ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ትለያቸዋለህ፤ እነርሱም የእኔ ይሆናሉ።
15“ሌዋውያኑን ካነጻሓቸውና እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህ ካቀረብሃቸው በኋላ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጣሉ፤ 16እነርሱም ሙሉ በሙሉ የእኔ እንዲሆኑ የተሰጡኝ እስራኤላውያን ናቸው፤ ከማንኛዪቱም እስራኤላዊት በተወለደ በኵር ወንድ ልጅ ምትክ የራሴ እንዲሆኑ ወስጃቸዋለሁ። 17ከሰውም ሆነ ከእንስሳ በእስራኤል የተወለደ ማንኛውም በኵር ተባዕት የእኔ ነው፤ በግብጽ የነበረውን በኵር ሁሉ በመታሁ ጊዜ የእኔ እንዲሆኑ ለይቻቸዋለሁ። 18በእስራኤል በተወለዱት ተባዕት በኵሮች ሁሉ ምትክም ሌዋውያኑን ወስጃለሁ። 19እስራኤላውያንን ወክለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት እንዲያከናውኑና እስራኤላውያን ወደ ተቀደሰው ስፍራ ቢቀርቡ እንዳይቀሠፉ ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፣ ከእስራኤላውያን ሁሉ መካከል ሌዋውያኑን ስጦታ አድርጌ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻቸዋለሁ።”
20ሙሴና አሮን እንዲሁም የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በሌዋውያኑ አደረጉ። 21ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሶቻቸውንም ዐጠቡ፤ ከዚያም አሮን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፤ እንዲነጹም ማስተስረያ አደረገላቸው። 22ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በአሮንና በልጆቹ ኀላፊነት ሥር ሆነው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት ለማከናወን ገቡ። እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት አስፈላጊውን በሌዋውያኑ አደረጉ።
23 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 24“ሌዋውያንን የሚመለከተው ደንብ ይህ ነው፤ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ለመሳተፍ ሃያ ዐምስት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንዶች ይመጣሉ፤ 25ዕድሜያቸው ዐምሳ ዓመት ሲሞላ ግን መደበኛ አገልግሎታቸውን ይተዉ፤ ዳግም ሥራ አይሥሩ። 26ከዚያ በኋላ ወንድሞቻቸው በመገናኛው ድንኳን ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ያግዟቸዋል እንጂ ራሳቸው መሥራት የለባቸውም። ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የምታሰማራቸው በዚህ መልኩ ነው።”

Currently Selected:

ዘኍልቍ 8: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ