ፊልጵስዩስ 3

3
በሥጋ አለመመካት
1ከዚህ በተረፈ ወንድሞቼ ሆይ፤ በጌታ ደስ ይበላችሁ! ያንኑ ደግሜ ብጽፍላችሁ፣ እኔ አይሰለቸኝም፤ ለእናንተም ይጠቅማችኋል። 2ከእነዚያ ውሾች ተጠንቀቁ፤ ክፋትን ከሚያደርጉና ሥጋን ከሚቈራርጡ ሰዎች ተጠበቁ። 3እኛ በእውነት የተገረዝን በእግዚአብሔር መንፈስ የምናመልክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የምንመካ፣ በሥጋም የማንታመን ነንና። 4ካስፈለገ እኔም በሥጋ የምመካበት አለኝ።
ማንም በሥጋ የሚመካበት ነገር ያለው ቢመስለው፣ እኔ እበልጠዋለሁ፤ 5በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፣ ከእስራኤል ዘር፣ ከብንያም ወገን የተወለድሁ ስሆን፣ ከዕብራውያንም ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ከተነሣ፣ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ 6ስለ ቅናት ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን አሳዳጅ ነበርሁ፤ ሕግን በመፈጸም ስለሚገኝ ጽድቅ ከሆነም፣ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።
7ነገር ግን ይጠቅመኝ የነበረውን ሁሉ አሁን ለክርስቶስ ስል እንደ ጕድለት ቈጥሬዋለሁ። 8ከዚህም በላይ ለርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋራ ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለርሱ ስል ሁሉን ዐጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ 9ሕግ በመጠበቅ የሚገኝ የራሴ ጽድቅ ኖሮኝ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን#3፥9 ወይም በክርስቶስ ባለ እምነት ይኸውም ከእግዚአብሔር የሚመጣ፣ ከእምነትም#3፥9 ከእምነትም በሆነ ጽድቅ በርሱ ዘንድ እንድገኝ ነው። 10ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ፣ በሥቃዩ ተካፋይ እንድሆንና በሞቱም እርሱን እንድመስል እመኛለሁ፤ 11ለሙታን ትንሣኤም እንድደርስ እናፍቃለሁ።
12ይህን ሁሉ አግኝቻለሁ ወይም ፍጹም ሆኛለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ። 13ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደ ያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ። 14እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ።
የጳውሎስን አርኣያነት መከተል
15እንግዲህ እኛ ብስለት ያለን ሁላችን ነገሮችን በዚህ ሁኔታ ማየት ይኖርብናል፤ በአንዳንድ ነገር የተለያየ አስተሳሰብ ቢኖራችሁ፣ እግዚአብሔር እርሱንም ይገልጥላችኋል። 16ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ።
17ወንድሞች ሆይ፤ የእኔን አርኣያነት በመከተል ከሌሎች ጋራ ተባበሩ፤ እኛ በሰጠናችሁ ምሳሌነት መሠረት የሚኖሩትንም አስተውሉ። 18ምክንያቱም ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንደ ነገርኋችሁ፣ አሁንም እንደ ገና፣ ያውም በእንባ እነግራችኋለሁ፤ ብዙዎች የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ። 19መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሐሳባቸው በምድራዊ ነገር ላይ ነው። 20እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን፤ 21እርሱም ሁሉን ለራሱ ባስገዛበት ኀይል፣ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።

Currently Selected:

ፊልጵስዩስ 3: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ