የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ምሳሌ 22

22
1መልካም ስም ከብዙ ብልጽግና ይመረጣል፤
መከበርም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል።
2ባለጠጋና ድኻ የሚጋሩት ነገር፣
እግዚአብሔር የሁላቸውም ፈጣሪ መሆኑ ነው።
3አስተዋይ ክፉን አይቶ ራሱን ይሸሽጋል፤
አላዋቂዎች ግን በዚያው ይቀጥላሉ፤ ይቀጡበታልም።
4ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣
ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል።
5በክፉዎች መንገድ ላይ እሾኽና ወጥመድ አለ፤
ነፍሱን የሚጠብቅ ግን ከእነዚህ ይርቃል።
6ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤#22፥6 ወይም አስጀምረው
በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።
7ባለጠጋ ድኻን ይገዛል፤
ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።
8ክፋትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፤
የቍጣውም በትር ይጠፋል።
9ቸር ሰው ራሱ ይባረካል፤
ምግቡን ከድኾች ጋራ ይካፈላልና።
10ፌዘኛን አስወጣው፤ ጠብ ይወገዳል፤
ጥልና ስድብም ያከትማል።
11የልብ ንጽሕናን ለሚወድድና ንግግሩም ሞገስ ላለው ሰው፣
ንጉሥ ወዳጁ ይሆናል።
12እግዚአብሔር ዐይኖች ዕውቀትን ይጠብቃሉ፤
የማይታመኑትን ሰዎች ቃል ግን እርሱ ከንቱ ያደርጋል።
13ሰነፍ፣ “አንበሳ በውጭ አለ፤
በጐዳና ላይ እገደላለሁ” ይላል።
14የአመንዝራ ሴት አፍ ጥልቅ ጕድጓድ ነው፤
እግዚአብሔር የተቈጣውም ይገባበታል።
15ቂልነት በሕፃን ልብ ታስሯል፤
የተግሣጽ በትር ግን ከርሱ ያርቅለታል።
16ሀብቱን ለማካበት ድኻን የሚበድል፣
ለባለጠጋም ስጦታ የሚያቀርብ፣ ሁለቱም ይደኸያሉ።
ሠላሳ የጠቢቡ ምክሮች
ምክር አንድ
17የጠቢባንን ቃል ልብ ብለህ ስማ፤
ልብህም ወደ ትምህርቴ ያዘንብል፤
18በልብህ ስትጠብቃቸው፣
ሁሉም በከንፈሮችህ ላይ የተዘጋጁ ሲሆኑ ደስ ይላልና።
19ስለዚህ መታመኛህ በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን፣
ዛሬ አንተን ራስህን አስተምርሃለሁ።
20የምክርና የዕውቀት ቃል የሆኑ፣
መልካም ሠላሳ ትምህርቶችን#22፥20 ወይም ትምህርቶችን ብቻ አልጻፍሁልህምን?
21ለላከህ ተገቢውን መልስ ትሰጥ ዘንድ፣
እውነተኛና የታመኑ ቃሎችን እንዳስተምርህ አይደለምን?
ምክር ሁለት
22ድኾች በመሆናቸው ብቻ ድኾችን አትበዝብዛቸው፤
ችግረኛውንም በአደባባይ አታንገላታው፤
23 እግዚአብሔር ይፋረድላቸዋልና፤
የሚቀሟቸውንም ይቀማቸዋል።
ምክር ሦስት
24ከግልፍተኛ ጋራ ወዳጅ አትሁን፤
በቀላሉ ቱግ ከሚልም ሰው ጋራ አትወዳጅ፤
25አለዚያ መንገዱን ትማራለህ፤
ራስህም ትጠመድበታለህ።
ምክር አራት
26በዋስትና ቃል እጅ አትምታ፤
ለብድር ተያዥ አትሁን፤
27የምትከፍለው ካጣህ፣
የምትተኛበት ዐልጋ ከሥርህ ይወሰድብሃል።
ምክር ዐምስት
28የቀድሞ አባቶችህ ያስቀመጡትን፣
የጥንቱን የወሰን ምልክት አታፋልስ።
ምክር ስድስት
29በሙያው ሥልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን?
በነገሥታት ዘንድ ባለሟል ይሆናል፤
አልባሌ ሰዎችን አያገለግልም።

Currently Selected:

ምሳሌ 22: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ