መዝሙር 2
2
መዝሙር 2
1አሕዛብ ለምን በቍጣ ተነሣሡ?
ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ?#2፥1 ዕብራይስጡ እንዲሁ ሲሆን፣ ሰብዓ ሊቃናት ግን ይቈጣሉ ይላል።
2የምድር ነገሥታት ተነሡ፤
ገዦችም በእግዚአብሔርና በመሲሑ#2፥2 ወይም የተቀባው ላይ
ሊመክሩ ተሰበሰቡ፤
3“ሰንሰለታቸውን እንበጥስ፣
የእግር ብረታቸውንም አውልቀን እንጣል” አሉ።
4በሰማይ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ይሥቃል፤
ጌታም ይሣለቅባቸዋል።
5ከዚያም በቍጣው ይናገራቸዋል፤
በመዓቱም ያስደነግጣቸዋል፤
6ደግሞም፣ “እኔ ግን በተቀደሰው ተራራዬ፣
በጽዮን ላይ የራሴን ንጉሥ ሾምሁ” ይላል።
7የእግዚአብሔርን ሕግ ዐውጃለሁ፤
እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “አንተ ልጄ ነህ፤
እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤#2፥7 ወይም …አባትህ ሆንሁ
8ለምነኝ፤
መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣
የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ።
9አንተም በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ፤#2፥9 ወይም በብረት ዘንግ ትሰባብራቸዋለህ
እንደ ሸክላ ዕቃ ታደቅቃቸዋለህ።”
10ስለዚህ እናንተ ነገሥታት ልብ በሉ፤
እናንተ የምድር ገዦችም፣ ተጠንቀቁ።
11 እግዚአብሔርን በፍርሀት አገልግሉት፤
ለርሱ በመንቀጥቀጥ ደስ ያሰኛችሁ።
12እንዳይቈጣና በመንገድ እንዳትጠፉ፣
ዝቅ ብላችሁ ልጁን ሳሙት፤
ቍጣው ፈጥኖ ይነድዳልና።
እርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.