መዝሙር 60
60
መዝሙር 60
60፥5-12 ተጓ ምብ – መዝ 108፥6-13
ለመዘምራን አለቃ፤ “የኪዳን ጽጌረዳ” በሚለው ቅኝት የሚዘመር፤#60 ርእስ የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ ወይም የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። በሰሜናዊ ምዕራብ መስጴጦምያና#60 ርእስ የአራማውያን ወይም የሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ነው። በማእከላዊ ሶርያ የሚኖሩትን አራማውያን#60 ርእስ በመካከለኛው ሶርያ የሚገኙት አራማውያንን የሚያመለክት ነው። በወጋቸው ጊዜ፣ ኢዮአብም ተመልሶ በጨው ሸለቆ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ኤዶማውያንን በፈጀ ጊዜ፣ ለትምህርት፤ የዳዊት ሚክታም#60 ርእስ የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ የሚያሳይ ወይም በሙዚቃ ውስጥ የሚጠቀሙበት ቃል ሳይሆን አይቀርም።።
1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጣልኸን፤ አንኰታኰትኸን፤
ተቈጣኸንም፤ አሁን ግን መልሰህ አብጀን።
2ምድሪቱን አናወጥሃት፤ ፍርክስክስ አደረግሃት፤
ትንገዳገዳለችና ስብራቷን ጠግን።
3ለሕዝብህ አበሳውን አሳየኸው፤
ናላ የሚያዞር የወይን ጠጅ እንድንጠጣም ሰጠኸን።
4ነገር ግን ከቀስት እንዲያመልጡ፣
ለሚፈሩህ ምልክት አቆምህላቸው። ሴላ
5ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፣
በቀኝ እጅህ ርዳን፤ መልስልንም።
6እግዚአብሔር ከመቅደሱ ተናገረ፤
“ደስ እያለኝ ሴኬምን እከፋፍላለሁ፤
የሱኮትንም ሸለቆ እለካለሁ።
7ገለዓድ የእኔ ነው፤ ምናሴ የእኔ ነው፤
ኤፍሬም የራስ ቍሬ ነው፤
ይሁዳም በትረ መንግሥቴ ነው።
8ሞዓብ የመታጠቢያ ገንዳዬ ነው፤
በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እወረውራለሁ፤
በፍልስጥኤም ላይ በድል አድራጊነት እጮኻለሁ።”
9ወደ ተመሸገችው ከተማ ማን ይወስደኛል?
ወደ ኤዶምያስ ማን ይመራኛል?
10አምላክ ሆይ፤ የጣልኸን አንተ አይደለህምን?
እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰራዊታችንም ጋራ አትወጣም።
11በጠላት ላይ ድልን አቀዳጀን፤
የሰው ርዳታ ከንቱ ነውና።
12በእግዚአብሔር ክንደ ብርቱ እንሆናለን፤
ጠላቶቻችንን የሚረጋግጥልን እርሱ ነውና።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.