የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 19

19
ሃሌ ሉያ
1ከዚህ በኋላ የብዙ ሰዎችን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤
“ሃሌ ሉያ!
ማዳን፣ ክብርና ኀይል የአምላካችን ነው፤
2ፍርዱ እውነትና ጽድቅ ነውና፤
በዝሙቷ ምድርን ያረከሰችውን፣
ታላቂቱን አመንዝራ ፈርዶባታል፤
ስለ ባሮቹም ደም ተበቅሏታል።”
3ደግሞም እንዲህ አሉ፤
“ሃሌ ሉያ!
ጢስ ከርሷ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።”
4ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ ሕያዋን ፍጡራን በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ ወድቀው ሰገዱ፤ እንዲህም አሉ፤
“አሜን፣ ሃሌ ሉያ!”
5ከዚህ በኋላ እንዲህ የሚል ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ፤
“እናንተ ባሮቹ ሁሉ፣
እርሱን የምትፈሩ፣
ታናናሾችና ታላላቆችም፣
አምላካችንን አመስግኑ!”
6ደግሞም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ፣ እንደ ኀይለኛ ወራጅ ውሃ ድምፅ፣ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ የሚመስል እንዲህ ሲል ሰማሁ፤
“ሃሌ ሉያ!
ሁሉን ቻይ ጌታ አምላካችን ነግሧልና።
7የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ፣
የእርሱም ሙሽራ ራሷን ስላዘጋጀች
ደስ ይበለን፤ ሐሤት እናድርግ፤
ክብርም እንስጠው።
8የሚያንጸባርቅና ንጹሕ፣
ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ እንድትለብስ ተሰጣት።”
ከተልባ እግር የተሠራው ቀጭን ልብስ የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነው።
9መልአኩም፣ “ ‘ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው’ ብለህ ጻፍ” አለኝ፤ ቀጥሎም፣ “እነዚህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃሎች ናቸው” አለኝ።
10እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋራ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ።
በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠው
11ከዚያም ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ “ታማኝና እውነተኛ” የሚባል ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በጽድቅ ይፈርዳል፤ ይዋጋልም። 12ዐይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከርሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም በርሱ ላይ ተጽፏል። 13እርሱ በደም የተነከረ ልብስ ለብሷል፤ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 14የሰማይም ሰራዊት ነጭ፣ ንጹሕና ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ ለብሰው፣ በነጫጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። 15ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ ከአፉ ወጣ፤ “በብረት በትርም ይገዛቸዋል።”#19፥15 መዝ 2፥9 እርሱም ሁሉን ቻይ የሆነውን የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣ ወይን መጭመቂያ ይረግጣል። 16በልብሱና በጭኑ ላይ እንዲህ የሚል ስም ተጽፏል፤
የነገሥታት ንጉሥና የጌቶችም ጌታ።
17ቀጥሎም አንድ መልአክ በፀሓይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፤ እርሱም በሰማይ መካከል ለሚበርሩ ወፎች ሁሉ እንዲህ ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ “ኑ፤ ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር እራት ተሰብሰቡ፤ 18የምትሰበሰቡትም የነገሥታትን ሥጋ፣ የጦር አዛዦችን ሥጋ፣ የብርቱ ሰዎችን ሥጋ፣ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ እንዲሁም የሰዎችን ሁሉ፣ ይኸውም የጌቶችንና የባሮችን፣ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ እንድትበሉ ነው።”
19ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሰራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሰራዊቱ ጋራ ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ። 20ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከርሱም ጋራ በፊቱ ምልክቶችን ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ። በእነዚህ ምልክቶች የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አሳተ። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ተጣሉ። 21የቀሩት ደግሞ በፈረሱ ላይ ከተቀመጠው አፍ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው በልተው ጠገቡ።

Currently Selected:

ራእይ 19: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ