የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 9

9
1ዐምስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀውንም ኮከብ አየሁ፤ ኮከቡም የጥልቁ ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። 2ጥልቁን ጕድጓድ በከፈተውም ጊዜ፣ ከውስጡ ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ያለ ጢስ ወጣ። ከጕድጓዱም በወጣው ጢስ ፀሓይና ሰማይ ጨለሙ። 3ከጢሱም አንበጦች ወጥተው በምድር ላይ ወረዱ፤ እንደ ምድር ጊንጦች ሥልጣን ያለ ሥልጣን ተሰጣቸው። 4እነርሱም የምድርን ሣር ወይም ማንኛውንም የለመለመ ተክል ወይም ዛፍ እንዳይጐዱ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ማኅተም በግምባራቸው ላይ የሌለባቸውን ሰዎች ብቻ እንዲጐዱ ተነገራቸው። 5እነርሱንም ዐምስት ወር ብቻ እንዲያሠቃዩአቸው እንጂ እንዲገድሏቸው ሥልጣን አልተሰጣቸውም፤ የሚሠቃዩትም ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ሲነድፍ እንደሚሰማው ዐይነት ሥቃይ ነው። 6በእነዚያ ቀኖች ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አያገኙትም፤ ለመሞትም ይመኛሉ፤ ነገር ግን ሞት ከእነርሱ ይሸሻል።
7አንበጦቹ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶች ይመስሉ ነበር፤ በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል የመሰለ ነገር ደፍተዋል፤ ፊታቸውም የሰው ፊት ይመስል ነበር፤ 8ጠጕራቸው የሴት ጠጕር፣ ጥርሳቸውም የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር። 9የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፎቻቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት የሚገሠግሡ የብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ድምፅ ይመስል ነበር። 10እንደ ጊንጥም ያለ፣ ጅራትና መንደፊያ ነበራቸው፤ ደግሞም ሰዎችን ዐምስት ወር የሚያሠቃዩበት ኀይል በጅራታቸው ላይ ነበር። 11በላያቸው ንጉሥ ነበራቸው፤ እርሱም የጥልቁ ጕድጓድ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ “አብዶን”፣ በግሪክ ደግሞ “አጶልዮን”#9፥11 አብዶን ወይም አጶልዮን ትርጕሙ አጥፊ ማለት ነው። ይባላል።
12የመጀመሪያው ወዮ ዐልፏል፤ እነሆ፤ ከዚህ በኋላ ገና ሌላ ሁለት ወዮዎች ይመጣሉ።
13ስድስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእግዚአብሔር ፊት ካለው በወርቅ ከተሠራው መሠዊያ ቀንዶች ድምፅ ሲመጣ#9፥13 ሲወጣ ማለት ነው። ሰማሁ፤ 14ድምፁም መለከት የያዘውን ስድስተኛውን መልአክ፣ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው” አለው። 15ከሰው ዘር አንድ ሦስተኛውን እንዲገድሉ፣ ለዚህች ሰዓትና ዕለት እንዲሁም ለዚህች ወርና ዓመት ተዘጋጅተው የነበሩት አራቱ መላእክት ተፈቱ። 16የፈረሰኛው ሰራዊት ብዛት ሁለት መቶ ሚሊዮን ነበር፤ ቍጥራቸውንም ሰማሁ።
17በራእዬ ያየኋቸው ፈረሶችና በላያቸውም የተቀመጡት ይህን ይመስሉ ነበር፤ ጥሩራቸው እንደ እሳት ቀይ፣ እንደ ያክንት ሰማያዊና እንደ ዲን ብጫ ነበር፤ የፈረሶቹ ራስ የአንበሶችን ራስ ይመስል ነበር። ከአፋቸውም እሳትና ጢስ፣ ዲንም ይወጣ ነበር። 18ከአፋቸው በወጡት፣ በሦስቱ መቅሠፍቶች፣ ማለት በእሳቱ፣ በጢሱና በዲኑ አንድ ሦስተኛው የሰው ዘር ተገደለ። 19የፈረሶቹ ኀይል በአፋቸውና በጅራታቸው ላይ ነበር፤ ጅራታቸውም እባብ ይመስል ነበር፤ ራስ ስላላቸው ጕዳት የሚያደርሱት በርሱ ነበር።
20በእነዚህ መቅሠፍቶች ሳይገደሉ የቀሩት ሰዎች አሁንም ከእጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትን እንዲሁም ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን፣ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከናስ፣ ከድንጋይና ከዕንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች ማምለክ አልተዉም፤ 21ደግሞም ከነፍስ ግድያቸው፣ ከጥንቈላ ሥራቸው፣ ከዝሙት ርኩሰታቸው ወይም ከስርቆት ተግባራቸው ንስሓ አልገቡም።

Currently Selected:

ራእይ 9: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ