ሮሜ 3

3
የእግዚአብሔር ታማኝነት
1ታዲያ አይሁዳዊ መሆን ጥቅሙ ምንድን ነው? መገረዝስ ምን ፋይዳ አለው? 2በየትኛውም መንገድ ጥቅሙ ብዙ ነው፤ ከሁሉ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃል በዐደራ የተሰጠው ለእነርሱ ነው።
3አንዳንዶች እምነት ባይኖራቸውስ? የእነርሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ ያሳጣዋልን? 4ከቶ አይሆንም! ይልቅስ እግዚአብሔር እውነተኛ፣ ሰው ሁሉ ግን ሐሰተኛ ይሁን፤
“በቃልህ ትጸድቅ፣
በፍርድም ፊት ረቺ ትሆን ዘንድ”#3፥4 መዝ 51፥4 ተብሎ ተጽፏልና።
5የእኛ ዐመፃ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አጕልቶ የሚያሳይ ከሆነ፣ ምን ማለት እንችላለን? እንደ ሰው ለመከራከር ያህል እግዚአብሔር በእኛ ላይ ቍጣውን በማምጣቱ ዐመፀኛ ነውን? እንደ ሰው ሲታሰብ ማለቴ ነው። 6ከቶ አይሆንም! እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ እግዚአብሔር በዓለም ላይ እንዴት ሊፈርድ ይችላል? 7“የእኔ ውሸተኛ መሆን የእግዚአብሔርን እውነተኛነት የሚያጐላ፣ ክብሩንም የሚጨምርለት ከሆነ፣ ኀጢአተኛ ተብዬ እስካሁን እንዴት ይፈረድብኛል?” በማለት ሊከራከር የሚችል ሰው ይኖር ይሆናል። 8ይህማ “በጎ እንዲመጣ ክፉ እንሥራ” ይላሉ በማለት አንዳንዶች እንደሚያስወሩብን ነው፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፍርድ ትክክለኛ ነው።
ማንም ጻድቅ አይደለም
9እንግዲህ ምን እንላለን? እኛ ከእነርሱ እንበልጣለንን?#3፥9 ወይም እንብሳለንን ከቶ አይደለም፤ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ፣ ሁሉም ከኀጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከስሰናቸዋል።
10እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤
“ጻድቅ ማንም የለም፤ አንድ እንኳ፤
11አስተዋይ የለም፤
እግዚአብሔርንም የሚሻ አንድም የለም።
12ሁሉም ተሳስተዋል፤
በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤
መልካም የሚያደርግ የለም፤
አንድ እንኳ።”#3፥12 መዝ 14፥1-3፤ 53:1-3፤ መክ 7፥20
13“ጕረሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤
በምላሳቸው ይሸነግላሉ።”#3፥13 መዝ 5፥9
“በከንፈሮቻቸው የእባብ መርዝ አለ።”#3፥13 መዝ 140፥3
14“አፋቸው ርግማንና ምሬት ሞልቶበታል።”#3፥14 መዝ 10፥7
15“እግሮቻቸው ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤
16በመንገዶቻቸው ጥፋትና ጕስቍልና ይገኛሉ፤
17የሰላምንም መንገድ አያውቁም።”#3፥17 ኢሳ 59፥7-8
18“በዐይናቸው ፊት ፈሪሀ እግዚአብሔር የለም።”#3፥18 መዝ 36፥1
19እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደ ሆነ፣ እናውቃለን፤ 20ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም ሥጋ ለባሽ በርሱ ፊት ሊጸድቅ አይችልም፤ ይልቁንም በሕግ አማካይነት ኀጢአትን እንገነዘባለን።
በእምነት የሚገኝ ጽድቅ
21አሁን ግን ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧል። 22ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው። ልዩነት የለም፤ 23ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል፤ 24በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል፤ 25በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተሰረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤#3፥25 በግሪኩ የማስተስረያ መሥዋዕት የሚለው ቃል የሚያመላክተው በቃል ኪዳኑ ታቦት የሚሸፈነውን ያለውን ስርየት ያመላክታል። ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ 26በአሁኑ ዘመን እግዚአብሔር ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን ለማሳየት ነው።
27ታዲያ ትምክሕት ወዴት ነው? እርሱማ ቀርቷል። በየትኛው ሕግ? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፤ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። 28ማንም ሰው ሕግን በመፈጸም ሳይሆን፣ በእምነት እንደሚጸድቅ እናረጋግጣለን። 29እግዚአብሔር የአይሁድ አምላክ ብቻ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን፤ የአሕዛብም አምላክ ነው፤ 30የተገረዘውን በእምነት፣ ያልተገረዘውንም በዚያው እምነት የሚያጸድቅ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና። 31ታዲያ እንዲህ ከሆነ ከእምነት የተነሣ ሕግን ዋጋ የሌለው እናደርግ ይሆን? ፈጽሞ አይደረግም፤ ሕጉን እናጸናለን እንጂ።

Currently Selected:

ሮሜ 3: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ