ሮሜ 6
6
ለኀጢአት መሞት፣ በክርስቶስ ሕያው መሆን
1እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ ኀጢአት እየሠራን እንኑር? 2ከቶ አይሆንም፤ ለኀጢአት ሞተናል፤ ታዲያ እንዴት አድርገን ከእንግዲህ በርሱ እንኖራለን? 3ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋራ አንድ እንድንሆን የተጠመቅን ሁላችን፣ ከሞቱ ጋራ አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? 4ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደ ተነሣ፣ እኛም እንዲሁ በአዲስ ሕይወት እንድንኖር በጥምቀት ሞተን ከርሱ ጋራ ተቀብረናል።
5በሞቱ ከርሱ ጋራ እንደዚህ ከተዋሐድን፣ በትንሣኤው ደግሞ በርግጥ ከርሱ ጋራ እንተባበራለን። 6ከእንግዲህ የኀጢአት ባሮች እንዳንሆን፣ የኀጢአት ሰውነት እንዲሻር#6፥6 ወይም ኀይል እንዳይኖረው አሮጌው ሰዋችን ከርሱ ጋራ እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ 7ምክንያቱም የሞተ ከኀጢአት ነጻ ወጥቷል።
8ከክርስቶስ ጋራ ከሞትን፣ ከርሱ ጋራ እንደምንኖር እናምናለን። 9ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷልና፣ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለን፤ ሞት ከእንግዲህ በርሱ ላይ ጕልበት አይኖረውም። 10በሞተ ጊዜ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኀጢአት ሞቷል፤ ነገር ግን በሕይወት መኖርን ለእግዚአብሔር ይኖራል።
11እንደዚሁም ለኀጢአት እንደ ሞታችሁ፣ ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቍጠሩ። 12ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ። 13ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 14ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና።
የጽድቅ ባሮች
15እንግዲህ ምን ይሁን? ከሕግ በታች ሳይሆን፣ ከጸጋ በታች በመሆናችን ኀጢአት እንሥራን? ከቶ አይሆንም! 16ራሳችሁን እንደ ባሪያ አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ለምትታዘዙት ለርሱ፣ ይኸውም ወደ ሞት ለሚወስደው ለኀጢአት ወይም ወደ ጽድቅ ለሚያደርሰው ለመታዘዝ ባሮች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? 17ነገር ግን የኀጢአት ባሮች የነበራችሁ ቢሆንም፣ ለተሰጣችሁለት ትምህርት በሙሉ ልብ የታዘዛችሁ በመሆናችሁ፣ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ 18ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ፣ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።
19በተፈጥሮ ደካሞች ስለ ሆናችሁ፣ በሰው ቋንቋ ይህን እላለሁ፤ ብልቶቻችሁን በባርነት ለርኩሰትና እየባሰ ለሚሄድ ክፋት ታቀርቡ እንደ ነበር፣ አሁን ደግሞ ወደ ቅድስና ለሚወስደው ጽድቅ ባሪያ አድርጋችሁ አቅርቡ። 20የኀጢአት ባሮች ሳላችሁ ከጽድቅ ነጻ ነበራችሁ። 21አሁን ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ? የዚያ ነገር ውጤት ሞት ነው! 22አሁን ግን ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር ባሮች ሆናችኋል፤ የምትሰበስቡትም ፍሬ ወደ ቅድስና ያመራል፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። 23የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ#6፥23 ወይም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካይነት የዘላለም ሕይወት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.