የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1

1
1በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ለመሆን ከተጠራው ከጳውሎስና ከወንድማችንም ከሶስቴንስ፦
2በቆሮንቶስ ከተማ ለምትገኘው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በውስጥዋም በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱትና ቅዱሳን እንዲሆኑ ለተጠሩት፥ እንደዚሁም በየቦታው ለእነርሱና ለእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ለሚጠሩት ሁሉ።
3ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ምስጋና ለእግዚአብሔር
4በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋውን ስለ ሰጣችሁ በእናንተ ምክንያት ሁልጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። 5በሁሉ ነገር በንግግርም ሆነ በዕውቀት በክርስቶስ በልጽጋችኋል። 6ስለ ክርስቶስ የነገርናችሁ ምስክርነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶአል። 7ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በመጠባበቅ ስትኖሩ ምንም ዐይነት መንፈሳዊ ስጦታ አይጐድልባችሁም፤ 8በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ያለነቀፋ ሆናችሁ ትገኙ ዘንድ እርሱ እስከ መጨረሻ ጸንታችሁ እንድትኖሩ ያደርጋችኋል። 9ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።
በክርስቲያኖች መካከል መለያየት ሊኖር እንደማይገባ
10ወንድሞቼ ሆይ! “መለያየት በመካከላችሁ አይኑር፤ ሁላችሁም ተስማምታችሁ በአንድ ሐሳብና በአንድ ዓላማ ጸንታችሁ ኑሩ” ብዬ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 11ወንድሞቼ ሆይ! በመካከላችሁ ጠብ መኖሩን ከቀሎኤ ቤተሰብ ሰምቼአለሁ። 12ይኸውም እናንተ እያንዳንዳችሁ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔ የአጵሎስ ነኝ፤ እኔ የጴጥሮስ ነኝ፤ እኔ የክርስቶስ ነኝ” ትላላችሁ። #ሐ.ሥ. 18፥24። 13ታዲያ ክርስቶስ ተከፋፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? ወይስ የተጠመቃችሁት በጳውሎስ ስም ነውን? 14እኔ ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ ማንንም ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። #ሐ.ሥ. 18፥8፤ 19፥29፤ ሮም 16፥23። 15ስለዚህ “በእኔ በጳውሎስ ስም ተጠምቃችኋል” ብሎ መናገር የሚችል የለም። 16(እርግጥ ነው፤ የእስጢፋኖስንም ቤተሰብ አጥምቄአለሁ፤ ከነዚህ ሌላ እኔ ያጠመቅሁት ሰው መኖሩን አላስታውስም፤) #1ቆሮ. 16፥15። 17ክርስቶስ የላከኝ የወንጌልን ቃል እንዳስተምር ነው እንጂ እንዳጠምቅ አይደለም፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር የወንጌልን ቃል የማስተምረው ከሰው ጥበብ በተገኘ ንግግር አይደለም።
ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጥበብና ኀይል መሆኑ
18የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሰዎች እንደ ሞኝነት ይቈጠራል፤ ለምንድን ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው።
19“የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤
የሊቃውንትንም ዕውቀት አስወግዳለሁ” ተብሎ ተጽፎአል። #ኢሳ. 29፥14።
20ታዲያ፥ ጥበበኛ የት አለ? የሕግ ምሁርስ የት አለ? ተመራማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት አድርጎት የለምን? #ኢዮብ 12፥17፤ ኢሳ. 19፥12፤ 33፥18፤ 44፥25።
21የዚህ ዓለም ሰዎች በገዛ ጥበባቸው እግዚአብሔርን ማወቅ እንዳይችሉ እግዚአብሔር በጥበቡ ዘጋባቸው፤ ነገር ግን እንደ ሞኝነት በሚቈጠረው እኛ በምናስተምረው ወንጌል የሚያምኑትን ለማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖአል። 22መቼም አይሁድ ተአምር ማየትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎች ደግሞ ጥበብን ይሻሉ። 23እኛ ግን ክርስቶስ ስለ እኛ መሰቀሉን እናስተምራለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናከያ ነው፤ ለግሪክ ሰዎች ደግሞ ሞኝነት ነው። 24ለተጠሩት ግን ለአይሁድም ሆነ ለግሪክ ሰዎች፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይልና የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። 25የእግዚአብሔር ሞኝነት ነው ተብሎ የሚታሰበው ነገር ከሰው ጥበብ ይበልጣል፤ የእግዚአብሔር ደካማነት ነው ተብሎ የሚታሰበውም ነገር ከሰው ኀይል ይበልጣል።
26ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔር በጠራችሁ ጊዜ ምን ዐይነት ሰዎች እንደ ነበራችሁ አስታውሱ፤ እንደ ሰው አስተሳሰብ ከእናንተ መካከል ብዙዎች ጥበበኞች ወይም ብርቱዎች ወይም ታላላቅ ሰዎች አልነበሩም። 27እግዚአብሔር ጥበበኞችን ለማሳፈር በዓለም እንደ ሞኞች የሚቈጠሩትን ሰዎች መረጠ፤ ብርቱዎችንም ለማሳፈር በዓለም እንደ ደካሞች የሚቈጠሩትን መረጠ፤ 28እግዚአብሔር በዓለም ሰዎች ዘንድ አሉ ተብለው የሚታዩትን ነገሮች እንደሌሉ ለማድረግ በዓለም የተዋረደና የተናቀ ከንቱም መስሎ የሚታየውን ነገር መረጠ። 29ይህንንም ያደረገው ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ ነው። 30እናንተን ግን እግዚአብሔር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አደረገ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ጥበባችን፥ ጽድቃችን፥ ቅድስናችንና ቤዛችን እንዲሆን አደረገው። 31እንግዲህ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈው “የሚመካ በጌታ ይመካ።” #ኤር. 9፥24።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ