አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 11
11
ሳኦል ዐሞናውያንን ድል ማድረጉ
1ከአንድ ወር በኋላ የዐሞን ንጉሥ ናዖስ በገለዓድ ግዛት በምትገኘው በያቤሽ ከተማ ላይ ሠራዊቱን በማዝመት ከበባት፤ የያቤሽም ሰዎች ናዖስን “ከእኛ ጋር የውል ስምምነት አድርግ፤ እኛም የአንተ አገልጋዮች እንሆናለን” አሉት።
2ናዖስም “ከእናንተ ጋር የውል ስምምነት ማድረግ የምችልበት አንድ ዐይነት ግዴታ አለ፤ ይኸውም የእያንዳንዱን ሰው ቀኝ ዐይን በማውጣት በእስራኤላውያን ላይ አሳፋሪ ውርደት አመጣለሁ” ሲል መለሰላቸው።
3የያቤሽ መሪዎችም “ወደ መላው የእስራኤል ምድር መልእክተኞች እስክንልክ ድረስ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ እኛን የሚታደገን ካጣን ለአንተ እጃችንን እንሰጣለን” አሉት።
4መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ ደረሱ፤ ወሬውንም በተናገሩ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። 5ሳኦል በዚህ ጊዜ ጥንድ በሬዎቹን ይዞ ከዋለበት እርሻ በመመለስ ላይ ነበር፤ እርሱም “ምንድን ነው ነገሩ? ሰው ሁሉ የሚያለቅሰው ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ፤ እነርሱም ከያቤሽ የመጡ መልእክተኞች የሚሉትን ወሬ ነገሩት። 6ሳኦልም ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በኀይል ወረደ፤ የሳኦልም ቊጣ እጅግ ገነፈለ። 7ጥንዱንም በሬዎች ወስዶ ቈራረጣቸው፤ የሥጋውንም ቊራጭ ሁሉ አስይዞ “ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ ወደ ጦርነት የማይወጣ ሰው ቢኖር በሬዎቹ እንደዚህ ይቈራረጡበታል!” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር መልእክተኞችን ወደ መላው የእስራኤል ምድር ላከ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን ፈራ፤ አንድም ሰው ሳይቀር ሁሉም በአንድነት ወጡ። 8ሳኦልም ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሰበሰባቸው፤ የቊጥራቸውም ብዛት ከእስራኤል የመጡት ሦስት መቶ ሺህ ሲሆን ከይሁዳ የመጡት ሠላሳ ሺህ ነበር። 9ከያቤሽ የመጡትንም መልእክተኞች “ነገ ከቀትር በፊት የምናድናቸው መሆኑን ለሕዝባችሁ ንገሩ” አሉአቸው። መልእክቱንም ለያቤሽ ሰዎች በነገሩ ጊዜ የያቤሽ ሰዎች እጅግ ተደሰቱ። 10የያቤሽም ሰዎች አሞናውያንን “ነገ እጃችንን ለእናንተ እንሰጣለን እናንተም በእኛ ላይ የምትፈልጉትን አድርጉ” አሉአቸው።
11በማግስቱ ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ከፈለ፤ ከማለዳ ጀምሮ ባለው ጊዜ በአሞናውያን ሰፈር ላይ አደጋ ጥለው ፀሐይ እስኪሞቅ ድረስ ፈጁአቸው፤ ከእልቂት የተረፉትም ተበታትነው ለየብቻቸው ሸሹ።
የሳኦል ንጉሥነት መረጋገጥ
12ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሳሙኤልን “ሳኦል በእኛ ላይ አይነግሥብንም ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው? እነርሱን አሳልፈህ ስጠንና እንግደላቸው!” አሉት።
13ሳኦል ግን “በዛሬው ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን ስላዳነ ማንም ሰው መገደል የለበትም” አለ። 14ሳሙኤልም “ሁላችንም ወደ ጌልጌላ እንሂድና ሳኦል ንጉሣችን መሆኑን እንደገና በይፋ እናረጋግጥ” አላቸው።
15ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልጌላ ሄደው በእግዚአብሔር ፊት የሳኦልን ንጉሥነት አጸደቁ፤ በእግዚአብሔርም ፊት የአንድነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ በዓሉንም ሳኦልና መላው ሕዝብ በታላቅ ደስታ አከበሩት።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997