አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2
2
የሐና ጸሎት
1ሐናም እንዲህ ብላ ጸለየች፦
“ልቤ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤
ክብሬም በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ ብሎአል፤
በማዳንህ ስለ ተደሰትኩ፤
በጠላቶቼ ላይ እሳለቃለሁ።
2“እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለም፤
እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤
አምላካችንን የሚመስልም መጠጊያ ምሽግ የለም፤
3እስቲ በመታበይ አትጓደዱ፤
የትምክሕት ንግግራችሁንም አስወግዱ፤
እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን ያውቃል፤
ሕዝብ የሚሠራውንም ሁሉ በፍርድ ይመዝናል።
4የኀያላን ቀስቶች ተሰበሩ፤
ደካሞች ግን ብርታትን አግኝተው ጠነከሩ፤
5ጠግበው የነበሩ ተርበው ለምግብ ተገዝተዋል፤
ተርበው የነበሩ ግን ጠግበዋል፤
መኻኒቱ ሰባት ወለደች፤
የብዙዎች ልጆች እናት የነበረችው ብቻዋን ቀረች።
6እግዚአብሔር ይገድላል፤ ያድናልም፤
ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ከሲኦልም ያወጣል፤
7እግዚአብሔር ያደኸያል፤ ያበለጽጋልም፤
ያዋርዳል፤ ከፍ፥ ከፍም ያደርጋል።
8እርሱ ድኾችን ከትቢያ ምስኪኖችንም ከዐመድ ላይ ያነሣል፤
ወደ ልዑላንም ደረጃ ከፍ ያደርጋቸዋል፤
የክብርም ዙፋን ያወርሳቸዋል
የምድርን መሠረቶች የሠራ እግዚአብሔር ነው፤
በእነርሱም ላይ ዓለምን የፈጠረ እርሱ ነው።
9“ሰው ድልን የሚያገኘው በኀይሉ ስላልሆነ
እግዚአብሔር የታማኞቹን እርምጃዎች ይጠብቃል፤
ክፉዎች ግን ወደ ጨለማ ይጣላሉ።
10እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ይደመሰሳሉ፤
ከሰማይም ያንጐደጒድባቸዋል፤
እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ይፈርዳል፤
ለንጉሥም ኀይልን ይሰጠዋል፤
ለመረጠውም ክብሩን ከፍ ከፍ ያደርግለታል።” #ሉቃ. 1፥46-55።
11ከዚህ በኋላ ሕልቃና በራማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ተመልሶ ሄደ፤ ሕፃኑ ሳሙኤልም በካህኑ ዔሊ ሥር ሆኖ እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።
የዔሊ ልጆች ክፉ አድራጎት
12የዔሊ ልጆች ምንም የማይረቡ ስድ አደጎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያከብሩም ነበር፤ 13ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደዚህ ነበር፦ ሰው ሁሉ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ሥጋው በመብሰል ላይ እያለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይቀርብ ነበር። 14እርሱም ሜንጦውን ወደ ድስቱ፥ ወይም ወደ ምንቸቱ፥ ወይም ወደ አፍላሉ፥ ወይም ወደ ቶፋው ይከተው ነበር፤ ሜንጦው የሚያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለራሱ ይወስደው ነበር፤ ይህንንም ድርጊት ወደ ሴሎ በሚመጡት እስራኤላውያን ሁሉ ላይ ያደርጉት ነበር። 15ከዚህም በቀር ጮማው ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መሥዋዕቱን ወደሚሠዋው ሰው መጥቶ “ካህኑ ያንተን የተቀቀለ ሥጋ ሳይሆን ጥሬ ሥጋ ስለሚፈልግ ለእርሱ እንድጠብስለት ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር።
16ሰውየውም “በመጀመሪያ ስቡን ያቃጥሉትና ከዚያ በኋላ የፈለግኸውን ትወስዳለህ” ቢለው፥ የካህኑ አገልጋይ “አይሆንም! አሁኑኑ ስጠኝ! እምቢ ብትል ግን በግድ እወስዳለሁ!” ይለው ነበር።
17በዚህም ዐይነት የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ስላቃለሉ የዔሊ ልጆች ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ከፍተኛ ነበር።
ሳሙኤል በሴሎ
18ሳሙኤል ግን ገና በልጅነቱ ከበፍታ የተሠራ ሸሚዝ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር፤ #2፥18 ሸሚዝ፦ በዕብራይስጡ ኤፉድ ይለዋል። ይህም ቃል በዕብራይስጡ ካህኑ ለሚለብሰው ልብስ ወይም በደረቱ ላይ ስለሚያደርገው ነገር መጠሪያ ነው። 19እናቱም በየዓመቱ ባልዋን ተከትላ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር። 20ዔሊም ሕልቃናን ከሚስቱ ከሐና ጋር በሚመርቅበት ጊዜ፥ ሕልቃናን “ለእግዚአብሔር የተለየ አድርጋችሁ በሰጣችሁት በዚህ ልጅ ፈንታ ከዚህቹ ሴት ሌሎችን ልጆች ይስጥህ!” ይለው ነበር።
ከዚያን በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር።
21እግዚአብሔርም ሐናን አስታወሳትና ሌሎች ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለደች፤ ወጣቱ ሳሙኤልም እግዚአብሔርን እያገለገለ አደገ።
ዔሊና ሁለቱ ልጆቹ
22እነሆ ዔሊ በዕድሜው አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በእስራኤላውያን ላይ የሚያደርጉት ክፉ ነገርና በድንኳኑ ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደሚያመነዝሩ ሰማ። 23ስለዚህም እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ይህን ክፉ ነገር ታደርጋላችሁ? የምታደርጉትን ክፉ ነገር ሁሉ ከእያንዳንዱ ሰው ሰምቼዋለሁ፤ 24ልጆቼ ሆይ! በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ስለ እናንተ የተሠራጨው ወሬ መልካም አይደለምና እንዲህ ያለ ክፉ ነገር አታድርጉ! 25አንድ ሰው ሌላውን ሰው ቢበድል፥ እግዚአብሔር በመታደግ ሊያድነው ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚበድል ሰው ማን ሊያማልደው ይችላል?”
ሆኖም እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ቊርጥ ውሳኔ ስላደረገ የዔሊ ልጆች የአባታቸውን ምክር አልሰሙም። #ሉቃ. 2፥52።
26ወጣቱ ሳሙኤል ግን በቁመት እያደገ፥ በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ ጸጋና ሞገስን እያገኘ ሄደ።
በዔሊ ቤተሰብ ላይ የተነገረ ትንቢት
27ከእግዚአብሔር የተላከ አንድ ነቢይ ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በፈርዖን ቤት ባሪያዎች በነበሩ ጊዜ ለቀድሞ አባትህ ለአሮን ራሴን ገለጥሁለት፤ 28እርሱንም ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፥ እጣን እንዲያጥን፥ በፊቴ ኤፉድ እንዲለብስ፥ የእኔ ካህን ይሆን ዘንድ መረጥሁት፤ ለቀድሞ አባትህ ልጆችም የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡትን የሚቃጠል መሥዋዕት ሰጠኋቸው። #ዘፀ. 28፥1-4፤ ዘሌ. 7፥35-36። 29በትእዛዜ መሠረት የሚቀርብልኝን መሥዋዕትና ቊርባን ለምን ታዋርዳላችሁ? ልጆችህ ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ምርጥ የሆነውን እየወሰዱ በመብላት ይወፍሩ ዘንድ እነርሱን ከእኔ ይበልጥ የምታከብራቸው ለምንድነው?’ 30ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘የአንተ ቤተሰብና የቀድሞ አባትህ ቤተሰብ ለዘለዓለም ያገለግሉኝ ዘንድ ቃል ገብቼ ነበር፤ አሁን ግን እንዲህ አይሆንም፤ የሚያከብሩኝን አከብራለሁ የሚንቁኝም ይናቃሉ። 31እነሆ፥ ከአንተ ቤተሰብ መካከል አንድም ሰው ወደ ሽምግልና ዕድሜ እንዳይደርስ አንተንና የአባቶችህን ቤተሰብ የማጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ ነው። 32እነሆ እኔ በምመለክበት ቦታ ብዙ ችግር ታያለህ፤ በእስራኤል ዘንድ በጎ ነገር የሚደረግ ቢሆንም ከአንተ ቤተሰብ መካከል ማንም ረጅም ዕድሜ የሚኖረው አይገኝም። 33በመሠዊያዬ ከምታገለግሉት ከእናንተ መካከል ሳላጠፋ የማስቀረው አንድ ሰው ዐይንህን በእንባ የሚያጠፋና ልብህን የሚያሳዝን ይሆናል፤ የቤተሰብህ አባሎች ሁሉ ግን በወጣትነት ዕድሜአቸው በሰይፍ ያልቃሉ፤ 34የሁለቱ ልጆችህ የሖፍኒና የፊንሐስ ዕድል ፈንታ ምልክት ይሆንሃል፤ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ። #1ሳሙ. 4፥11። 35ለእኔም እንደ ልቤና እንደ ሐሳቤ የሚያደርግ አንድ ታማኝ ካህን አስነሣለሁ፤ ለእርሱም የጸና ዘር እመሠርትለታለሁ፤ እኔ በቀባሁትም ንጉሥ ፊት ይመላለሳል። 36ከአንተ ዘሮች መካከል በሕይወት የሚተርፍ ሁሉ ወደዚያ ካህን ዘንድ እየሄደ ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት ከእርሱ ገንዘብና ምግብ ይለምናል፤ የዕለት ምግብ ብቻ ለማግኘትም ሲል ካህናትን በረዳትነት ማገልገል እንዲፈቀድለት ይለምናል።’ ”
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997