አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 6
6
የቃል ኪዳኑ ታቦት መመለስ
1የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በፍልስጥኤም ሰባት ወር ከቈየ በኋላ፥ 2ሕዝቡ ካህናታቸውንና አስማተኞቻቸውን ጠርተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁአቸው፤ “ስለ እግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ምን ማድረግ የሚሻለን ይመስላችኋል? ወደ ስፍራው እንዲመለስ ብናደርግ በምን ሁኔታ እንላከው? ዘዴውን ንገሩን” አሉአቸው።
3እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “የእስራኤልን አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት መልሳችሁ ለመላክ ብትፈልጉ፥ ስለ በደላችሁ የሚከፈል ስጦታ አብራችሁ መላክ ይገባችኋል፤ የቃል ኪዳኑ ታቦት ያለ ምንም ስጦታ ተመልሶ መሄድ የለበትም፤ በዚህም ዐይነት እናንተ ከሕመማችሁ ትፈወሳላችሁ፤ እርሱ እናንተን በብርቱ የቀጣበትንም ምክንያት ልታውቁ ትችላላችሁ።” 4ሕዝቡም፥ “ስለ በደል የሚከፈል ይሆን ዘንድ ከምን ዐይነት ስጦታ ጋር እንላከው?” ሲሉ ጠየቁ።
እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “በእባጩ አምሳል የተሠራ አምስት የወርቅ ጒልቻ፥ እንደ ፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ብዛት በአይጥ አምሳል የተሠራ አምስት የወርቅ ጉልቻ መሆን አለበት፤ በእናንተ ሁሉና በአምስቱ ገዢዎች ላይ የተላከው መቅሠፍት አንድ ዐይነት ነው። 5አገራችሁን ለማጥፋት በተላኩት አይጦችና እባጮች አምሳል እነዚህን ስጦታዎች ሠርታችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብር መስጠት አለባችሁ፤ ይህን ብታደርጉ ምናልባት እናንተን፥ አማልክታችሁንና ምድራችሁን የሚቀጣበትን መቅሠፍት ያነሣ ይሆናል፤ 6የግብጽ ንጉሥና ግብጻውያን እንዳደረጉት ስለምን ልባችሁን ታደነድናላችሁ? እስራኤላውያን የግብጽን ምድር ለቀው የወጡት፥ እግዚአብሔር ግብጻውያንን በብርቱ ከቀጣቸው በኋላ አልነበረምን? 7ስለዚህ አዲስ ሠረገላና ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት ጥጆችን አዘጋጁ፤ ጥጆቹን ጠምዳችሁ ሠረገላው የሚሳብበትን ጫፍ በቀንበሩ ላይ እሰሩት፤ እንቦሶቻቸውንም ወደ በረት መልሱ፤ 8የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት ወስዳችሁ በሠረገላው ላይ አኑሩ፤ ስለ በደላችሁም እንዲከፈል ከእርሱ ጋር ለመላክ የሠራችሁትን ልዩ ልዩ ወርቅ በሣጥን ውስጥ አስገብታችሁ በታቦቱ ጐን አስቀምጡ፤ ሠረገላውንም መንገድ አስይዛችሁ እንዲንቀሳቀስ ተዉት። 9ከዚህም በኋላ አካሄዱን ተመልከቱት፤ አቅጣጫው ወደ ቤትሼሜሽ ከተማ ያመራ እንደ ሆነ ይህን አሠቃቂ መቅሠፍት በእኛ ላይ የላከብን እግዚአብሔር መሆኑን ያመለክታል፤ ወደዚያ አቅጣጫ ባያመራ ግን መቅሠፍቱ የመጣብን በአጋጣሚ እንጂ እግዚአብሔር የላከብን አለመሆኑን እንገነዘባለን።”
10እነርሱም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ ሁለት ላሞች ወስደው ሠረገላ በታሰረበት ቀንበር ጠመዱአቸው፤ እንቦሶቻቸውንም ወደ በረት መልሰው ዘጉባቸው። 11የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስደው በአይጦችና በእባጮች አምሳል የተሠራ ወርቅ ከተሞላበት ሣጥን ጋር በሠረገላው ላይ አስቀመጡ፤ 12ላሞቹም መንገዱን ሳይለቁና ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳያዘነብሉ በቀጥታ ወደ ቤትሼሜሽ በማምራት ጒዞአቸውን ቀጠሉ፤ በሚሄዱበትም ጊዜ እምቧ ይሉ ነበር፤ አምስቱ የፍልስጤማውያን ገዢዎችም እስከ ቤትሼሜሽ ድንበር ድረስ በመከተል ሸኙአቸው።
13የቤትሼሜሽም ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር፤ ቀና ብለው በተመለከቱም ጊዜ ታቦቱን አዩ፤ ያንንም በማየታቸው እጅግ ደስ አላቸው። 14ሠረገላውም በቤትሼሜሽ ወደሚኖር ኢያሱ ተብሎ ወደሚጠራው ሰው እርሻ መጥቶ በትልቅ ቋጥኝ አጠገብ ሲደርስ ቆመ። ሕዝቡም የሠረገላውን እንጨት ፈለጡ፤ ላሞቹንም ዐርደው ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡአቸው። 15ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦትና ከእርሱ ጋር የነበረውን ወርቅ የሞላበት ሣጥን አንሥተው በታላቁ ቋጥኝ ላይ አስቀመጡ፤ የቤትሼሜሽም ሰዎች የሚቃጠልና ሌላውንም መሥዋዕት ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ 16አምስቱም የፍልስጥኤም ገዢዎች ይህን ሁሉ ሲመለከቱ ቈይተው በዚያው ቀን ወደ ዔቅሮን ተመለሱ።
17ስለ በደላቸው የሚከፈሉ ስጦታዎች ይሆኑ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ለእግዚአብሔር የላኩአቸው በእባጮች አምሳል የተሠሩ አምስት የወርቅ እንክብሎች አሽዶድ፥ ጋዛ፥ አስቀሎና፥ ጋትና ዔቅሮን ተብለው በሚጠሩት ከተሞቻቸው ስም የተላኩ ነበሩ፤ 18እንዲሁም ከተላኩት መካከል በተመሸጉ ከተሞችና ቅጽር ባልተሠራላቸው መንደሮች ሆነው አምስቱ የፍልስጥኤም ገዢዎች በሚያስተዳድሩት በእያንዳንዱ ከተማ ስም በአይጥ አምሳል የተሠሩ አምስት የወርቅ እንክብሎች ነበሩ። በቤትሼሜሽ በሚኖረው በኢያሱ እርሻ ውስጥ የእግዚአብሔርን ታቦት ያኖሩበትም ታላቅ ቋጥኝ እስከ ዛሬ ድረስ ምስክር ሆኖ ይታያል።
19የታቦቱን ውስጣዊ ክፍል በመመልከታቸው እግዚአብሔር ተቈጥቶ ከቤት ሼሜሽ ሰዎች መካከል ሰባ ሰዎችን ገደለ፤ እግዚአብሔርም ይህን ሁሉ እልቂት በመካከላቸው በማድረጉ የቤት ሼሜስ ሰዎች በማዘን አለቀሱ።
የቃል ኪዳኑ ታቦት በቂርያትይዓሪም
20ስለዚህም የቤትሼሜሽ ሰዎች “በዚህ ቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ማን መቆም ይችላል? ታቦቱስ ከእኛ ወጥቶ ወደ ማን ይሄዳል?” አሉ። 21በቂርያትይዓሪም ወደሚኖሩትም ሕዝብ መልእክተኞችን ልከው “ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኛ አምጥተዋታልና መጥታችሁ ውሰዱት” አሉ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997