1 ወደ ጢሞቴዎስ 3
3
ኤጲስ ቆጶሳት (የቤተ ክርስቲያን መሪዎች)
1አንድ ሰው “ኤጲስ ቆጶስ (የቤተ ክርስቲያን መሪ) ለመሆን ቢፈልግ ክቡር ሥራን ይመኛል” የሚለው ቃል እውነተኛ ነው። 2ስለዚህ አንድ ኤጲስ ቆጶስ (የቤተ ክርስቲያን መሪ) ነቀፋ የሌለበት፥ አንዲት ሚስት ብቻ ያገባ፥ በመጠን የሚኖር፥ ራሱን የሚገዛ፥ በሥርዓት የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር ችሎታ ያለው፥ 3የማይሰክር፥ ክርክር የማይወድ፥ ገር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ገንዘብን የማያፈቅር፥ 4የገዛ ራሱን ቤተሰብ በደንብ ማስተዳደር የሚችል፥ ልጆቹ በተገቢ በአክብሮት የሚታዘዙለት መሆን ይገባዋል። 5ሰው የገዛ ራሱን ቤተሰብ ማስተዳደር የማይችል ከሆነ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ማስተዳደር እንዴት ይችላል? 6በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ እንደ ተፈረደበት እንዳይፈረድበት አዲስ አማኝ ኤጲስ ቆጶስ አይሁን። 7በነቀፋና በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ በማያምኑ ሰዎች ዘንድ መልካም ስም እንዲኖረው ያስፈልጋል። #ቲቶ 1፥6-9።
ስለ ዲያቆናት
8እንዲሁም ዲያቆናት የተከበሩና በቃላቸው የሚጸኑ፥ ብዙ የወይን ጠጅ የማይጠጡ፥ ለገንዘብ የማይስገበገቡ መሆን አለባቸው፤ 9እንዲሁም የእምነትን ምሥጢር በንጹሕ ኅሊና የሚጠብቁ መሆን ይገባቸዋል፤ 10እነርሱም በመጀመሪያ ይፈተኑ፤ ከዚያም በኋላ ነቀፋ የሌለባቸው ሆነው ከተገኙ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ። 11እንዲሁም ሚስቶቻቸው የተከበሩ፥ ሰውን የማያሙ፥ በመጠን የሚኖሩ፥ በሁሉም ነገር ታማኞች መሆን ይገባቸዋል። 12ዲያቆናት እያንዳንዳቸው የአንዲት ሚስት ባል መሆን ይገባቸዋል፤ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውንም በመልካም ይዞታ ማስተዳደር አለባቸው። 13በዲቁና ሥራ መልካም አገልግሎት የሚያበረክቱ ከፍ ያለ ማዕርግ ያገኛሉ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስላለውም እምነት የመናገር ድፍረት ይኖራቸዋል።
ታላቁ ምሥጢር
14-15በቅርብ ጊዜ ለመምጣት ተስፋ ባደርግም እንኳ ምናልባት ከመምጣት የዘገየሁ እንደ ሆነ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንና የእውነት ዐምድ መሠረት በሆነው በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ሰዎች ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ታውቅ ዘንድ ይህን መመሪያ እጽፍልሃለሁ። 16የሃይማኖታችን ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ እርሱም እግዚአብሔር፦
“ሰው ሆኖ ተገለጠ፤
እውነተኛነቱ በመንፈስ ታወቀ፥
ለመላእክት ታየ፥
ለሕዝቦች ሁሉ ተሰበከ፥
በዓለም ያሉ ሰዎች አመኑበት፥
በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ” የሚል ነው።
Currently Selected:
1 ወደ ጢሞቴዎስ 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997