የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ጢሞቴዎስ 5

5
ስለ መበለቶች የተሰጠ ምክር
1ሽማግሌን እንደ አባት አድርገህ ምከረው እንጂ አትገሥጸው፤ ወጣቶች ወንዶችን እንደ ወንድሞች፥ 2አሮጊቶችን እንደ እናቶች አድርገህ ተመልከታቸው፤ እንዲሁም ወጣት ሴቶችን እንደ እኅቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ተመልከታቸው።
3በእርግጥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች አክብራቸው። 4ማንኛይቱም ባል የሞተባት ሴት ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት እነዚህ ልጆች አስቀድመው ለቤተሰቦቻቸው የመጠንቀቅን፥ ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው ብድር የመመለስን መንፈሳዊ ግዴታ ይማሩ፤ ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። 5በእርግጥ መበለት የሆነችና ብቻዋን የምትኖር፥ ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ አድርጋ ሌሊትና ቀን የእግዚአብሔርን ርዳታ በመለመን በጸሎት ጸንታ ትኖራለች። 6የዚህን ዓለም ደስታ ብቻ የምትወድ መበለት ግን በቁሟ የሞተች ናት። 7ያለ ነቀፋ እንዲኖሩም እነዚህን ትምህርቶች ስጣቸው። 8ለራሱ ዘመዶች፥ ይልቁንም ለቅርብ ቤተሰቦቹ የማያስብ ሃይማኖቱን የካደ ነው፤ እንዲያውም ከማያምን ሰው እንኳ የባሰ ክፉ ነው።
9ከስድሳ ዓመት በታች የሆነችን ባልዋ የሞተባትን ሴት በመበለቶች መዝገብ አትጻፍ፤ ደግሞም አንድ ባል ብቻ ያገባች እንድትሆን ያስፈልጋል። 10እንዲሁም ልጆችን በሚገባ በማሳደግ፥ እንግዳን በመቀበል፥ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፥ የተቸገሩትን በመርዳትና ማንኛውንም በጎ ሥራ ሁሉ በማከናወን ለመልካም ሥራም ሁሉ የተጋች መሆን አለባት።
11ባሎቻቸው የሞቱባቸው በዕድሜ ያልገፉ ሴቶች ሥጋዊ ምኞታቸው አሸንፎአቸው ለክርስቶስ ያላቸው ፍቅር ሲቀነስ ባል ማግባት ስለሚፈልጉ እነርሱን በመበለቶች መዝገብ አትጻፋቸው። 12እነዚህ ሴቶች በመጀመሪያ ለክርስቶስ የገቡትን ቃል በማፍረሳቸውም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ። 13ደግሞም ሥራ መፍታትን ይማራሉ፤ ሥራ መፍታት ብቻ ሳይሆን በየሰዉ ቤት እየዞሩ ሰውን የሚያሙ፥ በሰው ነገር የሚገቡና መናገር የማይገባቸውን የሚናገሩ ይሆናሉ። 14ስለዚህ በዕድሜአቸው ያልገፉ መበለቶች እንዲያገቡ፥ ልጆችን እንዲወልዱ፥ ቤታቸውንም በሚገባ እንዲያስተዳድሩ እመክራለሁ፤ በዚህ ዐይነት ጠላት ለስም ማጥፋት ምክንያት ያጣል። 15ከዚህ በፊትም አንዳንድ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ሰይጣንን በመከተል ከእምነት መንገድ ወጥተዋል። 16አንዲት አማኝ የሆነች ሴት በቤትዋ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ቢኖሩአት የቤተ ክርስቲያን ሸክም እንዳይሆኑ እርስዋ ትርዳቸው፤ በዚህ ዐይነት ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ ረዳት የሌላቸውን ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች መርዳት ትችላለች።
17ቤተ ክርስቲያንን በደንብ የሚያስተዳድሩ፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር ይገባቸዋል፤ 18ቅዱስ መጽሐፍ “እህል የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፤” እንዲሁም “ለሠራተኛው ደመወዝ ይገባዋል” ይላል። #ዘዳ. 25፥4፤ ማቴ. 10፥10፤ ሉቃ. 10፥7። 19ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ካልመሰከሩበት በቀር በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ላይ የሚቀርበውን ክስ አትቀበል። #ዘዳ. 17፥6፤ 19፥15። 20ሌሎች እንዲፈሩ ኃጢአት የሚሠሩትን በሰዎች ሁሉ ፊት ገሥጽ።
21በምታደርገው ነገር ሁሉ አንዱን ከሌላው ሳታበላልጥ ወይም ለማንም ሳታዳላ ይህን ምክሬን ሁሉ እንድትፈጽም በእግዚአብሔርና በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት ዐደራ እልሃለሁ። 22እጆችህን በመጫን ማንንም ለመሾም አትቸኲል፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ እንጂ ከሌሎች ሰዎች ጋር በኃጢአት አትተባበር።
23ስለ ሆድህ ሕመምና ስለ ዘወትር ደዌህ ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ።
24የአንዳንድ ሰዎች ኃጢአት ግልጥ በመሆኑ አስቀድሞ ፍርዱን ያመለክታል፤ የሌሎች ሰዎች ኃጢአት ግን የሚገለጠው ዘግየት ብሎ ነው። 25እንዲሁም መልካም ሥራ ግልጥ ነው፤ ግልጥ ያልሆነውም እንኳ ተሰውሮ አይቀርም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

YouVersion የእርስዎን ተሞክሮ ግላዊ ለማድረግ ኩኪዎችን ይጠቀማል። የእኛን ድረ ገጽ በመጠቀም፣ በግለሰብነት መመሪያችን ላይ እንደተገለጸው የእኛን የኩኪዎች አጠቃቀም ተቀብለዋል