ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9
9
ዳዊትና መፊቦሼት
1አንድ ቀን ዳዊት “ስለ ዮናታን ስል ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤተሰብ ከሞት የተረፈ ሰው አለን?” ብሎ ጠየቀ። #1ሳሙ. 20፥15-17።
2ከሳኦል ቤተሰብ ጺባ የሚባል አንድ አገልጋይ ነበረ፤ እርሱም ወደ ዳዊት እንዲሄድ ተነገረው፤ ዳዊትም “አንተ ጺባ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
ጺባም “ጌታ ሆይ! እነሆ አገልጋይህ ነኝ!” ሲል መለሰ።
3ንጉሡም “እግዚአብሔር የሚፈቅደውን ቸርነት የማሳየው ከሳኦል ቤተሰብ ከሞት የተረፈ ሰው አለን?” ሲል ጺባን ጠየቀው። #2ሳሙ. 4፥4።
ጺባም “ከዮናታን ወንዶች ልጆች አንዱ አሁንም በሕይወት አለ፤ እርሱም እግረ ሽባ ነው” ሲል መለሰ።
4ንጉሡም “የት ነው ያለው?” ሲል ጠየቀ።
ጺባም “በሎደባር በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ሲል መለሰ። 5ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት መፊቦሼትን ከሎደባር ከዓሚኤል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው።
6የሳኦል የልጅ ልጅ፥ የዮናታን ልጅ መፊቦሼት በመጣ ጊዜ በዳዊት ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት አክብሮቱን ገለጠ።
ዳዊትም “መፊቦሼት!” ሲል ጠራው።
መፊቦሼትም “ጌታ ሆይ! እነሆ አገልጋይህ ነኝ!” ሲል መለሰ።
7ዳዊትም “አይዞህ አትፍራ! ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግልሃለሁ፤ የአያትህ የሳኦል ይዞታ የነበረውን መሬት ሁሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም በማእዴ ተቀምጠህ ትመገባለህ” አለው።
8መፊቦሼትም በአክብሮት እጅ ነሥቶ “የሞተ ውሻ ልመመስል ለእኔ ለአገልጋይህ ይህን ያኽል ቸርነት የምታደርግልኝ ለምንድን ነው?”
9ከዚህ በኋላ ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ጺባን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “የሳኦልና የቤተሰቡ ንብረት የነበረውን ማናቸውንም ነገር የጌታህ የልጅ ልጅ ለሆነው ለመፊቦሼት እሰጣለሁ፤ 10አንተ፥ ወንዶች ልጆችህና አገልጋዮችህ ለጌታህ ለሳኦል ቤተሰብ ምድሪቱን አርሳችሁ ምግብ ይሆናቸው ዘንድ መከሩን አገቡላቸው፤ የጌታህ የልጅ ልጅ መፊቦሼት ግን ዘወትር በገበታዬ የሚቀርብ ተመጋቢ ይሆናል፤” ጺባ ዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆችና ኻያ አገልጋዮች ነበሩት።
11ጺባም “ንጉሥ ሆይ! እኔ አገልጋይህ አንተ ያዘዝከውን ሁሉ እፈጽማለሁ” ሲል መለሰ።
በዚህ ዐይነት መፊቦሼት ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ተቈጥሮ በንጉሥ ገበታ እየቀረበ ይመገብ ነበር። 12መፊቦሼት ሚካ የተባለ ወጣት ልጅ ነበረው፤ የጺባ ቤተሰብ አባሎች በሙሉ የመፊቦሼት አገልጋዮች ሆኑ፤ 13ስለዚህ ሁለቱም እግሮቹ ሽባ የሆኑት መፊቦሼት በንጉሡ ገበታ እየቀረበ በመመገብ የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሆነ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997