የሐዋርያት ሥራ 14
14
ጳውሎስና በርናባስ በኢቆንዮን
1በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኲራብ ገቡ፤ በዚያም ብዙ አይሁድና ከአሕዛብ እጅግ ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። 2ያላመኑት አይሁድ ግን አሕዛብን አነሣሥተው በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር አደረጉ። 3ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ የጌታን ነገር በድፍረት እየተናገሩ እዚያ ብዙ ጊዜ ቈዩ፤ ጌታም ተአምራትና ድንቅ ነገሮች በእነርሱ እጅ እንዲደረጉ ሥልጣን በመስጠት፥ የእርሱ የጸጋ ቃል እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጥ ነበር። 4የከተማው ነዋሪዎች ግን፥ በሁለት ተከፍለው ግማሹ ከአይሁድ ጋር ግማሹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ።
5አሕዛብና አይሁድ ከአለቆቻቸው ጋር ሆነው ጳውሎስንና በርናባስን ሊያንገላቱአቸውና በድንጋይ ሊወግሩአቸው ፈለጉ፤ 6ጳውሎስና በርናባስ ይህን ባወቁ ጊዜ ልስጥራና ደርቤ ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሽተው ሄዱ። 7እዚያም ወንጌልን ሰበኩ።
ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራና በደርቤ
8በልስጥራ እግሩ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ከተወለደ ጀምሮ ሽባ ስለ ነበር በእግሩ ሄዶ አያውቅም፤ 9ይህ ሰው ጳውሎስ በሚናገርበት ጊዜ ተቀምጦ ያዳምጥ ነበር፤ ጳውሎስ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተና ለመዳን የሚያበቃው እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ 10“ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” ሲል በታላቅ ድምፅ ተናገረ፤ ሰውየውም ብድግ አለና መራመድ ጀመረ። 11ሰዎቹም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” በማለት በሊቃኦንያ ቋንቋ ተናገሩ። 12በርናባስንም “ድያ” አሉት፤ ዋናው ተናጋሪ ጳውሎስ ስለ ነበረ እርሱን “ሄርሜን” አሉት። 13ከከተማው ውጪ ያለው የድያ ቤተ መቅደስ ካህን ኮርማዎችንና የአበባ ጒንጒኖችን ወደ ከተማው በር አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ለጳውሎስና ለበርናባስ መሥዋዕት ሊያቀርብላቸው ፈለገ።
14ሐዋርያቱ ጳውሎስና በርናባስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ሕዝቡ ሮጡና እየጮኹ እንዲህ አሉ፦ 15“እናንተ ሰዎች ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እንደ እናንተ ሰዎች ነን፤ እኛ እዚህ የመጣነው እናንተ ከዚህ ከከንቱ ነገር ሁሉ ርቃችሁ ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርንና በውስጣቸው የሚገኙትን ሁሉ ወደ ፈጠረው ወደ ሕያው አምላክ እንድትመለሱ መልካም ዜና ልናበሥርላችሁ ነው፤ #ዘፀ. 20፥11፤ መዝ. 146፥6። 16ባለፉት ዘመኖች ሕዝቦች ሁሉ በገዛ ራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ እግዚአብሔር ትቶአቸዋል፤ 17ይሁን እንጂ እርሱ እንዴት ያለ ቸር አምላክ መሆኑን የሚመሰክር መልካም ሥራ ማድረጉን አላቋረጠም፤ ከሰማይ ዝናብን አዘነበላችሁ፤ የመከር ወራትንም ሰጣችሁ፤ በምግብና በደስታ ልባችሁን አረካ።” 18ሐዋርያት ይህን ያኽል ቢናገሩም እንኳ ሕዝቡ ለእነርሱ መሥዋዕት እንዳያቀርብ ያስተዉት በብዙ ችግር ነው።
19አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን ወደዚያ መጥተው ሕዝቡን አሳደሙና ጳውሎስን በድንጋይ እንዲወግሩት አደረጉ፤ የሞተ መስሎአቸውም ጐትተው ከከተማ አወጡት። 20ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በዙሪያው በቆሙ ጊዜ ጳውሎስ ተነሣና ወደ ከተማ ገባ፤ በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ።
ጳውሎስና በርናባስ በሶርያ ወደምትገኘው አንጾኪያ መመለሳቸው
21ጳውሎስና በርናባስ በደርቤ ወንጌልን አስተምረው ብዙ ሰዎችን አማኞች ካደረጉ በኋላ በልስጥራና በኢቆንዮን አልፈው በጵስድያ ወደምትገኘው አንጾኪያ ሄዱ። 22በእነዚያም አገሮች ሁሉ አማኞች በእምነታቸው እንዲጸኑ በማበረታታትና በመምከር “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ብዙ መከራ መቀበል አለብን” እያሉ አስተማሩአቸው። 23በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው፤ ከጾሙና ከጸለዩም በኋላ ላመኑበት ጌታ ዐደራ ሰጡአቸው።
24በጵስድያም አልፈው ወደ ጵንፍልያ ሄዱ፤ 25በጴርጌም የእግዚአብሔርን ቃል ካስተማሩ በኋላ ወደ አጣልያ ሄዱ፤ 26ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ ዐደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ።
27እዚያም በደረሱ ጊዜ አማኞችን በአንድነት ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ ያደረገውን ሁሉና አሕዛብም እንዲያምኑ እንዴት አድርጎ በር እንደ ከፈተላቸው ነገሩአቸው። 28እዚያም ከአማኞች ጋር ብዙ ጊዜ ቈዩ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 14: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997