የሐዋርያት ሥራ 3
3
የሽባው መፈወስ
1አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፤ 2እዚያ “ውብ” እየተባለ የሚጠራ በር ነበር፤ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የሆነውን አንድ ሰው ሰዎች በየቀኑ እያመጡ እዚያ ያስቀምጡት ነበር፤ እርሱ እዚያ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት ይለምን ነበር። 3ይህ ሰው ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው። 4እነርሱም ሰውየውን ትኲር ብለው አዩትና ጴጥሮስ “ወደ እኛ ተመልከት!” አለው። 5እርሱም ምጽዋት የሚሰጡት መስሎት ትኲር ብሎ አያቸው። 6ጴጥሮስ ግን “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ተራመድ!” አለው። 7ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውኑ እግሩና ቊርጭምጭሚቱ በረታ። 8ብድግ ብሎም ቆመ፤ እየተራመደም ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ እየተራመደና እየዘለለም እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። 9ሰዎቹም ሁሉ ሲራመድና እግዚአብሔርን ሲያመሰግን አዩት። 10“ውብ በር” እየተባለ በሚጠራው በቤተ መቅደሱ በር አጠገብ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በእርሱ ላይም በተደረገው ነገር ይገረሙና ይደነቁ ጀመር።
ጴጥሮስ በቤተ መቅደስ ያደረገው ንግግር
11የዳነው ሰው ከጴጥሮስና ከዮሐንስ አልለይም በማለት ይዞአቸው ሳለ ሰዎቹ ተደንቀው “የሰሎሞን መመላለሻ” ወደሚባለው ስፍራ ወደ እነርሱ ሮጠው ሄዱ፤ 12ጴጥሮስም ሰዎቹን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በዚህ ነገር ስለምን ትደነቃላችሁ? ስለምንስ ትኲር ብላችሁ ታዩናላችሁ? እኛ በራሳችን ኀይል ወይም በራሳችን መልካም ሥራ ይህን ሰው እንዲራመድ ያደረግነው ይመስላችኋልን? 13የአባቶቻችን የአብርሃም፥ የይስሐቅና፥ የያዕቆብ አምላክ ልጁን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እርሱን በጲላጦስ ፊት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስም ሊለቀው ቢፈልግ እንኳ ‘አንፈልግም’ አላችሁ። #ዘፀ. 3፥15። 14እናንተ ቅዱሱንና ጻድቁን ‘አንፈልገውም’ ብላችሁ አንድ ነፍሰ ገዳይ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ። #ማቴ. 27፥15-23፤ ማር. 15፥6-14፤ ሉቃ. 23፥13-23፤ ዮሐ. 19፥12-15። 15ሕይወት ሰጪ የሆነውንም ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሞት አስነሣው፤ ስለዚህ ነገር እኛ ምስክሮች ነን። 16ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው ድኖ የበረታው በኢየሱስ ስም በተገኘው እምነት ነው፤ በኢየሱስ ስም በማመኑም በሁላችሁ ፊት ሙሉ ጤንነት አግኝቶአል።
17“አሁንም ወንድሞቼ ሆይ! በኢየሱስ ላይ ያደረጋችኹትን ነገር እናንተም እንዳለቆቻችሁ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት ዐውቃለሁ። 18እግዚአብሔር ግን አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ ‘መሲሑ መከራ መቀበል አለበት’ ያለው ቃል በዚህ ዐይነት እንዲፈጸም አደረገ። 19እንግዲህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስላችሁ ንስሓ ገብታችሁ ወደ ጌታ ተመለሱ፤ 20ከእግዚአብሔርም ዘንድ የምትታደሱበት ዘመን ይመጣላችኋል፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለእናንተ የመረጠውን መሲሕ ኢየሱስን ይልክላችኋል። 21እርሱም በሰማይ የሚቈየው እግዚአብሔር አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው ዓለም ሁሉ እስኪታደስ ድረስ ነው። 22ሙሴም እንዲህ ብሎአል፦ ‘ጌታ አምላክህ እኔን እንዳስነሣኝ እንዲሁ ከወንድሞቻችሁ መካከል ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙ፤ #ዘዳ. 18፥15፤18። 23ያን ነቢይ የማይሰማ ሁሉ ከሕዝብ ተለይቶ ፈጽሞ ይጠፋል።’ #ዘዳ. 18፥19። 24ቀጥሎም ከሳሙኤል ጀምሮ የነበሩ ነቢያት ሁሉ፥ ስለዚህ ዘመን እንዲሁ ተናግረዋል። 25እናንተ የነቢያት ወራሾች ናችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ’ ብሎ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ። #ዘፍ. 22፥18። 26ስለዚህ እግዚአብሔር ልጁን የላከው በመጀመሪያ ለእናንተ ነበር፤ ይህንንም ያደረገው እያንዳንዳችሁን ከክፉ መንገዳችሁ በመመለስ እንዲባርካችሁ ነው።”
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997