ትንቢተ አሞጽ 7
7
የአንበጣን መምጣት የሚያመለክት ራእይ
1ጌታ እግዚአብሔር ይህን ራእይ አሳየኝ፤ እነሆ የንጉሡ የመከር እህል ከታጨደ በኋላ እንደገና ገቦ ሆኖ በበቀለው እህል ላይ እግዚአብሔር የአንበጣ መንጋ እንዲፈለፈል አደረገ፤ 2አንበጦቹም የምድሩን ልምላሜ ሁሉ ግጠው እንደ በሉት ባየሁ ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ የሕዝብህን በደል ይቅር በል! ሕዝብህ እስራኤል ዐቅም ስለሌላቸው እንዴት ተቋቊመው መኖር ይችላሉ?”
3እግዚአብሔርም ራርቶላቸው “ይህ ያየኸው ነገር አይፈጸምም!” አለኝ።
የቅጣት እሳት መምጣቱን የሚያመለክት ራእይ
4ጌታ እግዚአብሔር የገለጠልኝ ሌላውም ራእይ ይህ ነው፤ እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር የእሳት ቅጣት ፍርድ አስተላለፈ፤ እሳቱም ባሕሩን በልቶ ካደረቀው በኋላ ምድርን ማቃጠል ጀመረ። 5በዚያን ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ እሳቱ እንዲቆም አድርግ! ሕዝብህ እስራኤል ዐቅም የሌላቸው ስለ ሆኑ እንዴት ተቋቊመው መኖር ይችላሉ?”
6እግዚአብሔርም ራርቶላቸው “ይህም ደግሞ አይፈጸምም” አለኝ።
ቱምቢ (የግድግዳን ቀጥተኛነት ማስተካከያ)
7እግዚአብሔር ሌላ ራእይ ገለጠልኝ፤ እነሆ እግዚአብሔር በቱምቢ ተስተካክሎ በተሠራ ቅጽር አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ በእጁም ቱምቢ ይዞ ነበር፤ 8እርሱም “አሞጽ ሆይ! የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ።
እኔም “ቱምቢ ነው” አልኩ።
ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “በቱምቢ ተስተካክሎ እንዳልተሠራ ቅጽር ሕዝቤ እስራኤል ጠማሞች ሆነው ስለ ተገኙ ይህ ቱምቢ የእስራኤልን ጠማማነት ማሳያ ምሳሌ ነው፤ ሳልቀጣቸውም አላልፍም። 9የይስሐቅና የልጅ ልጆቹ ከፍተኛ የመስገጃ ቦታዎች ይፈራርሳሉ፤ የእስራኤልም የተቀደሱ ቦታዎች ፈራርሰው ወና ይሆናሉ፤ የኢዮርብዓምን መንግሥት ፈጽሞ አጠፋለሁ።”
አሞጽና አሜስያስ
10የቤትኤል ካህን የሆነው አሜስያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም ላከ፦ “እነሆ አሞጽ በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሆኖ በአንተ ላይ እያሤረብህ ነው፤ ሕዝቡ የእርሱን ንግግር ሊታገሥ አይችልም። 11እርሱም ‘ኢዮርብዓም በጦርነት ይሞታል፤ የእስራኤልም ሕዝብ ከሀገራቸው ተማርከው ይሄዳሉ’ ይላል።”
12አሜስያስ አሞጽን እንዲህ አለው፦ “አንተ ባለ ራእይ! ወደ ይሁዳ ተመልሰህ ሂድና በዚያ ትንቢት እየተናገርክ መተዳደሪያህን አግኝ። 13ቤትኤል ግን የንጉሡ መስገጃና የሕዝቡም ቤተ መቅደስ ስለ ሆነች በዚህች ቦታ ዳግመኛ ትንቢት እንዳትናገር።”
14አሞጽም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ እኮ የመንጋዎች እረኛና የሾላ ፍሬ ተንከባካቢ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ 15ነገር ግን የበግ መንጋ ከምጠብቅበት ቦታ ወስዶ ‘ሂድ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር’ ብሎ ያዘዘኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው። 16አሁንም እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ስማ፤ አንተ ‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፤ የይስሐቅ ዘሮች የሆኑትንም የእስራኤልን ሕዝብ አትስበክ’ ብለህ ከልክለኸኛል። 17ስለዚህም አሜስያስ ሆይ! እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል፦ ‘ሚስትህ በከተማይቱ አመንዝራ ትሆናለች፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በጦርነት ይሞታሉ፤ ርስትህንም ባዕዳን በገመድ ለክተው ይከፋፈሉታል፤ አንተም በአሕዛብ ምድር ትሞታለህ፤ የእስራኤልም ሕዝብ ያለ ጥርጥር ተማርከው ከአገራቸው ይወሰዳሉ።’ ”
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 7: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997