ኦሪት ዘዳግም 30
30
ወደ እግዚአብሔር በመመለስ የሚገኝ በረከት
1“እኔ ዛሬ በፊትህ በበረከትና በመርገም መካከል ምርጫን ሰጥቼሃለሁ፤ እግዚአብሔር በሕዝቦች መካከል በበተነህ ቦታ ሆነህ ብታስታውሰው 2አንተ ከዘሮችህ ጋር ወደ እግዚአብሔር ብትመለስና ዛሬ እኔ ለምሰጥህ ለእግዚአብሔር ሕጎች ከልብ ታዛዥ ሆነህ ብትገኝ፥ 3አምላክህ እግዚአብሔር ምሕረት ያደርግልሃል፤ በአሕዛብ መካከል አንተን ከበታተነበት ስፍራ ሁሉ መልሶ በማምጣት እንደገና ያበለጽግሃል። 4እስከ ምድር ዳርቻ ተበታትነህ የምትኖር ብትሆን እንኳ አምላክህ እግዚአብሔር በአንድነት በመሰብሰብ መልሶ ያመጣሃል፤ 5በዚህም ዐይነት የቀድሞ አባቶችህ የነበሩበትን ምድር እንደገና ትወርሳለህ፤ እርሱም ከቀድሞ አባቶችህ ይበልጥ ባለጸጋና ቊጥርህ የበዛ እንድትሆን ያደርጋል። 6አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለልጆችህ ታዛዥ ልብ ይሰጣል፤ ስለዚህም እርሱን በፍጹም ልብህ ትወደዋለህ፤ በዚያችም ምድር በሕይወት ትኖራለህ። 7እነዚህንም መርገሞች ሁሉ አንተን በሚጠሉህና በሚጨቊኑህ ጠላቶችህ ላይ ይመልስባቸዋል፤ 8አንተም እንደገና ለእርሱ ታዛዥ ትሆናለህ፤ ዛሬ እኔ የምሰጥህንም የእርሱን ትእዛዞች ትጠብቃለህ፤ 9በምትሠራው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያበለጽግሃል፤ ልጆችህን፤ እንስሶችህንና የምድርህን ሰብልና ፍሬ ያበዛልሃል፤ እግዚአብሔር የቀድሞ አባቶችህን በማበልጸግ ደስ ይለው እንደ ነበር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋል። 10ይህንንም የሚያደርገው በዚህ የሕግ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉትን ትእዛዞችና ሕጎች በመጠበቅ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር የተመለስክ እንደ ሆነ ነው።
በሕይወትና በሞት መካከል የሚደረግ ምርጫ
11“ዛሬ እኔ የምሰጥህ ትእዛዝ በጣም ከባድ ወይም ከአንተ የራቀ አይደለም፤ 12‘እርሱን ሰምተን እንታዘዘው ዘንድ ማን ወጥቶ ያመጣልናል’ ብለህ እንዳትጠይቅ፥ ይህ ሕግ የሚገኘው በሰማይ አይደለም። 13‘እርሱን ሰምተን እንታዘዘው ዘንድ ከባሕር ማዶ ተሻግሮ ማን ሊያመጣልን ይችላል?’ ብለህ እንዳትጠይቅ፥ እርሱ የሚገኘው ከባሕር ማዶ አይደለም። 14ቃሉ ለእናንተ በጣም ቅርብ ነው፤ ትጠብቀውም ዘንድ በአፍህና በልብህ ውስጥ ይገኛል። #ሮም 10፥6-8።
15“ዛሬ እኔ ሕይወትንና መልካምነትን ወይም ሞትንና ክፋትን እንድትመርጥ ሰጥቼሃለሁ፤ 16ዛሬ እኔ ለማዝህ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ትእዛዞች ታዛዥ ብትሆን፥ በሕጉ ብትመራ፥ ትእዛዞቹን፥ ሕጎቹንና ሥርዓቱን ብትጠብቅ በሕይወት ትኖራለህ፤ ትበዛለህም፤ አምላክህ እግዚአብሔርም በምትገባበት ምድር ይባርክሃል። 17ነገር ግን ልብህን ከእግዚአብሔር አርቀህ ቃሉን የማትሰማ ብትሆን፥ ለሌሎችም አማልክት ልትሰግድላቸውና ልታመልካቸው ብትባክን፥ 18እንደምትደመሰስ እነሆ፥ ዛሬ አስጠነቅቅሃለሁ። ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሳት ምድር ለረጅም ዘመን አትኖርም። 19እነሆ፥ እኔ በሕይወትና በሞት መካከል፥ በእግዚአብሔር በረከትና መርገም መካከል ምርጫ እሰጣችኋለሁ፤ በምታደርጉትም ምርጫ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ ምስክር አድርጌ እጠራለሁ፤ ስለዚህም እናንተና ዘሮቻችሁ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጡ። 20አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፤ ለእርሱም ታዛዥ ሁን፤ በእርሱም እመን፤ ይህም ለአንተ ሕይወት ከመሆኑም በላይ ለቀድሞ አባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ቃል በገባላቸው መሠረት ገብተህ በምትኖርባት ምድር ለረጅም ዘመን ትኖራለህ።” #ዘፍ. 12፥7፤ 26፥3፤ 28፥13።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 30: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997