የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ አስቴር 1

1
ንግሥት አስጢን ለንጉሥ አርጤክስስ ትእዛዝ ያሳየችው እምቢተኛነት
1ንጉሥ አርጤክስስ ከሕንድ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያሉትን መቶ ኻያ ሰባት አገሮችን ይገዛ ነበር። 2በዚያን ጊዜ ንጉሡ አርጤክስስ ሱሳ በምትገኘው ቤተ መንግሥቱ ይኖር ነበር።
3አርጤክስስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖችና አስተዳዳሪዎች ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በግብዣውም ላይ የፋርስና የሜዶን ጦር አዛዦች፥ አገረ ገዢዎችና የክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ተገኝተው ነበር።
4ንጉሡም ለስድስት ወራት ያኽል የመንግሥቱን የሀብት ብዛትና የንጉሣዊውን ግርማ ሞገስና ክብር በይፋ እንዲታይ አደረገ።
5ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ የመናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ለሚኖሩ ሁሉ ለሀብታሞችም፥ ለድኾችም፥ እንደገና ሌላ ግብዣ አደረገ፤ በቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ውስጥ የተደረገውም ያ ግብዣ አንድ ሳምንት ሙሉ ቈየ። 6የአትክልት ቦታውም ከነጭ ጥጥ በፍታ በተሠሩ ሰማያዊ ቀለም ባላቸው መጋረጃዎች የተጌጠ ነበር፤ መጋረጃዎቹም ከሐምራዊ በፍታ በተሠሩና የብር ቀለበት በተበጀላቸው ገመዶች በዕብነ በረድ ምሰሶዎች ላይ ተንጠልጥለው ነበር፤ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ድንክ አልጋዎችም ነጭና ቀይ፥ ቢጫና ሰማያዊ ቀለማትን በሚፈነጥቅ የዕብነ በረድ ወለል ላይ ተደርድረው ነበረ። 7አንዱ ከሌላው በማይመሳሰል በልዩ ልዩ የወርቅ ዋንጫ መጠጥ ይታደል ነበር፤ የንጉሡ የወይን ጠጅ ብዛት ስለ ነበረው የወይን ጠጁ በገፍ እንዲሰጥ አደረገ፤ 8ንጉሡም ማንኛውም ሰው እንደየባህሉ የሚፈልገውን ያኽል መጠጣት ይችል ዘንድ ለቤተ መንግሥቱ አገልጋዮች ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር።
9ይህ በዚህ እንዳለ ንግሥት አስጢን ደግሞ በበኲልዋ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ለሴት ወይዛዝርት ግብዣ አድርጋ ነበር።
10ግብዣው በተጀመረ በሰባተኛው ቀን ንጉሥ አርጤክስስ በወይን ጠጅ ረክቶ ደስ ባለው ጊዜ መሁማን፥ ቢዝታ፥ ሐርቦና፥ ቢግታ፥ አባግታ፥ ዜታርና ካርካስ ተብለው የሚጠሩትን ጃንደረቦች የሆኑትን ሰባቱን የእልፍኝ አገልጋዮቹን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ 11“ንግሥት አስጢን ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳና ዘውድ ጭና ወደዚህ እንድትመጣ አድርጉ” አላቸው፤ ንጉሡ ይህንን ያደረገበት ምክንያት ንግሥት አስጢን እጅግ የተዋበች ስለ ነበረች ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖችና ለእንግዶቹ ሁሉ እንድትታይ ፈልጎ ነበር። 12ነገር ግን ይህን የንጉሡን ትእዛዝ ለንግሥት አስጢን በነገሩአት ጊዜ ወደ ንጉሡ ፊት ለመቅረብ እምቢ አለች፤ ይህም ሁኔታ ንጉሡን እጅግ አስቈጣው።
13ሕግና ባህልን በሚመለከት ጉዳይ፥ ብልኅ አማካሪዎችን መጠየቅ በንጉሡ ዘንድ የተለመደ ነገር ስለ ነበር፥ በዚህም ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባው ይመክሩት ዘንድ አማካሪዎቹን አስጠራ። 14ዘወትር የሚያማክሩትም ካርሸና፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ታርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማርሰናና መሙካን ተብለው የሚጠሩ በመንግሥቱ አመራር ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰባቱ የፋርስና የሜዶን ሹማምንት ነበሩ። 15ንጉሡም እነዚህን አማካሪዎች “እኔ ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስጢንን ያመጡ ዘንድ በማዘዝ አገልጋዮቼን ብልክባት እርስዋ እምቢ ብላ ቀርታለች! ታዲያ፥ በእርስዋ ላይ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ሕጉ ምን ይላል?” ሲል ጠየቃቸው።
16ከዚህ በኋላ ከአማካሪዎቹ አንዱ የሆነው መሙካን እንዲህ ሲል የውሳኔ ሐሳብ አቀረበ፤ “በመሠረቱ ንግሥት አስጢን ያዋረደችው ንጉሡን ብቻ ሳይሆን ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖችና እንዲያውም በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉትን ወንዶች ሁሉ ጭምር ነው። 17ከእንግዲህ ወዲህ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ውስጥ የምትኖር ማንኛዋም ሴት፥ ንግሥት አስጢን ያደረገችውን ሁሉ ስትሰማ ባልዋን በንቀት ዐይን መመልከት ትጀምራለች፤ እነርሱም በበኩላቸው ‘ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስጢንን ወደ እርሱ እንድትመጣ ቢያስጠራት እምቢ ብላው ቀርታ የለምን?’ ይላሉ። 18የፋርስና የሜዶን መንግሥት ባለሥልጣኖች ሚስቶች ይህን ንግሥቲቱ የፈጸመችውን አሳፋሪ ድርጊት በሚሰሙበት ጊዜ ዛሬውኑ ፀሐይ ሳትጠልቅ በባሎቻቸው ላይ መዘባነን ይጀምራሉ፤ በየሀገሩ የሚገኙ ሚስቶችም ባሎቻቸውን ማክበርን ይተዋሉ፤ ባሎችም ከሚስቶቻቸው ጋር መጣላት ሊኖርባቸው ነው። 19ንጉሥ ሆይ! እንግዲህ መልካም ፈቃድህ ቢሆን፥ ንግሥት አስጢን ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ ፊት መቅረብ ከቶ እንዳይፈቀድላት የሚገልጥ ውሳኔህን በዐዋጅ አስተላልፍ፤ ይህም ውሳኔ ከቶ የማይለወጥ ሆኖ ለዘለዓለም ይጸና ዘንድ በፋርስና በሜዶን ሕግ ውስጥ እንዲመዘገብ ትእዛዝ አስተላልፍ፤ የአስጢንንም የንግሥትነት ማዕርግ ከእርስዋ ለተሻለች ለሌላ ሴት ስጥ። 20አንተ የምታስተላልፈውም ዐዋጅ እጅግ ታላቅ በሆነው በዚህ በንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ ግዛት ሁሉ በይፋ በሚነገርበት ጊዜ እያንዳንድዋ ሴት ባለጸጋም ይሁን ወይም ድኻ ባልዋን በአክብሮት ትመለከታለች።”
21ንጉሡና ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖች ሁሉ ይህን ሐሳብ በደስታ ተቀበሉት፤ ንጉሡም መሙካን ያቀረበውን ምክር በሥራ ላይ አዋለ። 22ስለዚህም ንጉሡ “እያንዳንዱ ባል የቤቱ አባወራ ሆኖ በአዛዥነት የመናገር መብቱ የተጠበቀ ይሁን!” የሚል ትእዛዝ በየቋንቋውና በየአጻጻፍ ሥርዓቱ ተዘጋጅቶ ወደያንዳንዱ አገር እንዲተላለፍ አደረገ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ