የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 16

16
እግዚአብሔር ለሕዝቡ መናንና ድርጭቶችን ማዝነቡ
1መላው የእስራኤል ማኅበር ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ወር፥ በዐሥራ አምስተኛው ቀን፥ ከኤሊም ተነሥተው በሲና እና በኤሊም መካከል ወዳለው “ሲን” ተብሎ ወደሚጠራው ምድረ በዳ መጡ። 2በዚያም ምድረ በዳ ሁሉም ተባብረው በሙሴና በአሮን ላይ በማጒረምረም እንዲህ አሉ፦ 3“ምነው በግብጽ ሳለን እግዚአብሔር በገደለን ኖሮ፥ በዚያ ሌላው ቢቀር ሥጋም ሆነ ሌላ ምግብ የፈለግነውን ያኽል መመገብ እንችል ነበረ፤ እናንተ ግን ሁላችንም በራብ እንድናልቅ ወደዚህ በረሓ አወጣችሁን።”
4እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ እኔ ለሁላችሁም የሚበቃ ምግብ ከሰማይ ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡ በየዕለቱ ወጥተው ለዚያው ቀን የሚበቃቸውን ምግብ ይሰብስቡ፤ በዚህ ዐይነት እኔ የምሰጣቸውን መመሪያ ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ። #ዮሐ. 6፥31። 5በስድስተኛው ቀን ግን፥ ከሌሎቹ ዕለቶች በአንዱ ቀን የሚሰበስቡትን እጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።”
6ስለዚህ ሙሴና አሮን ለመላው የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አሉ፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬይቱ ምሽት ታውቃላችሁ፤ 7በማለዳ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ፤ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ሰምቶአል፤ በእኛ ላይ የምታጒረመርሙት እኛ ማን ነን?” 8ከዚህም በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፦ “በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ስለ ሰማ በማታ የምትበሉትን ሥጋና በማለዳ ደግሞ የፈለጋችሁትን ያኽል እንጀራ የሚሰጣችሁ እግዚአብሔር ነው፤ እኛ ምንድን ነን? በእኛ ላይ ስታጒረመርሙ በእግዚአብሔር ላይ ማጒረምረማችሁ ነው።”
9ሙሴ አሮንን፦ “እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ስለ ሰማ፥ መላው የእስራኤል ማኅበር መጥታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቁሙ ብለህ ንገራቸው” አለው። 10አሮንም ለመላው ማኅበር በተናገረ ጊዜ ፊታቸውን ወደ በረሓው አዞሩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር በደመና ተገለጠ፤ 11እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12“እስራኤላውያን በእኔ ላይ ማጒረምረማቸውን ሰምቼአለሁ፤ ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በዛሬው ምሽት ፀሐይ ከመጥለቅዋ በፊት ምግብ የሚሆናችሁን ሥጋ ታገኛላችሁ፤ በማለዳም የምትፈልጉትን ያኽል እንጀራ ታገኛላችሁ፤ በዚያን ጊዜም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ።’ ”
13በምሽትም ብዙ ድርጭቶች እየበረሩ መጥተው ሰፈሩን ሸፈኑት፤ በማለዳ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ነበረ፤ 14ጤዛውም ከተነነ በኋላ ደቃቅና ስስ የሆነ ነገር በበረሓማው ምድር ላይ ታየ፤ እርሱም በምድር ላይ ያረፈ ዐመዳይ ይመስል ነበር። 15እስራኤላውያን ባዩት ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው “ይህ ነገር ምንድን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። #1ቆሮ. 10፥3።
ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህ እንድትበሉት እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው፤ 16ከእናንተ እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያኽል ብቻ እንዲሰበስብ እግዚአብሔር አዞአል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አንድ ኪሎ ተኩል ይውሰድ።” #16፥16 አንድ ኪሎ ተኩል (ጎሞር)፦ ሁለት ሊትር ወይም አንድ ኪሎ ተኩል ነው።
17እስራኤላውያንም እንደዚሁ አደረጉ፤ አንዳንዶቹ ብዙ አንዳንዶቹ ጥቂት ሰበሰቡ፤ 18በሰፈሩትም ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አላነሰበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው ልክ የሚበቃውን ያኽል ነበር። #2ቆሮ. 8፥15። 19ሙሴም “ማንም ለዕለት ከሚያስፈልገው አስበልጦ ለነገ ማስተረፍ የለበትም” አለ። 20አንዳንዶቹ የሙሴን ቃል ባለመስማት ለዕለቱ ከሰበሰቡት ከፍለው አሳደሩ፤ በማግስቱም ጠዋት ተልቶ ተገኘ፤ በስብሶም ሸተተ፤ ሙሴም እጅግ ተቈጣቸው። 21በየማለዳው እያንዳንዱ የሚበቃውን ያኽል ይሰበስብ ነበር፤ ፀሐይ ከሞቀ በኋላ ግን በመሬት ላይ የቀረው ሁሉ ይቀልጥ ነበር።
22በስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሦስት ኪሎ ይሰበስቡ ነበር፤ የማኅበሩ መሪዎች ሁሉ መጥተው ስለ ምግቡ ለሙሴ ነገሩት፤ 23እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “የነገው ዕለት ለእርሱ ተለይቶ የተቀደሰ የዕረፍት ቀን እንዲሆን እግዚአብሔር አዞአል፤ ስለዚህ ዛሬውኑ የምትጋግሩትን ጋግሩ፤ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፤ የተረፈው ተከፍሎ ለነገ ይቀመጥ።” #ዘፀ. 20፥8-11። 24ሙሴም እንዳዘዛቸው የተረፈውን ለሚቀጥለው ቀን አስቀመጡ፤ እርሱም አልሸተተም ወይም አልተላም። 25ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ ሰንበት ስለ ሆነና እርሱም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ቀን በመሆኑ በዛሬው ዕለት ምግቡን በሜዳ ላይ አታገኙም። 26ስለዚህ ስድስት ቀን በተከታታይ ይህን ምግብ ሰብስቡ፤ የዕረፍት ቀን በሆነው በሰባተኛው ቀን ግን ምንም ምግብ አይኖርም።”
27በሰባተኛው ቀን ከሕዝቡ መካከል ጥቂት ሰዎች ምግብ ለመሰብሰብ ወጡ፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም። 28ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እናንተ ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን መፈጸም እምቢ የምትሉት እስከ መቼ ነው? 29እኔ አንድ የዕረፍት ቀን ሰጥቻችኋለሁ፤ ዘወትር በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚበቃ ምግብ ስለምሰጣችሁ በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ከቤት ሳይወጣ፥ ባለበት ስፍራ ሁሉ ዕረፍት አድርጎ ይዋል።” 30ስለዚህ ሕዝቡ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።
31እስራኤላውያን ያን ምግብ “መና” ብለው ጠሩት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ፍሬ ነጭ የሆነ ነበር፤ ጣዕሙም ከማር ጋር እንደ ተጋገረ ቂጣ ነበር። #16፥31 መና፦ በዕብራይስጥ “ይህ ምንድን ነው” እንደማለት ነው። #ዘኍ. 11፥7-8። 32ሙሴም “እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ ከእርሱ አንድ አንድ ኪሎ ተኩል ሙሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ይጠበቅ።” አለ። 33ሙሴም አሮንን “አንድ የሸክላ ዕቃ ወስደህ አንድ ኪሎ ተኩል በሚይዝ መስፈሪያ መና አኑርበት፤ ለመጪውም ትውልድ በእግዚአብሔር ፊት ተጠብቆ እንዲኖር አድርግ” አለው። #ዕብ. 9፥4። 34እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት አሮን ለመጪው ትውልድ ተጠብቆ እንዲኖር መናውን በኪዳኑ ታቦት ፊት አኖረው። 35እስራኤላውያንም ወደሚኖሩባት ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪደርሱ ድረስ ለአርባ ዓመት ሙሉ ይህን መና ተመገቡ። 36በዚያን ጊዜ መደበኛ መስፈሪያዎች ኢፍና ጎሞር ይባሉ ነበሩ። ኢፍ ዐሥራ አምስት ኪሎ ሲመዝን ጎሞር አንድ ኪሎ ተኩል ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ