ኦሪት ዘጸአት 18
18
የትሮ ሙሴን ጐበኘ
1የምድያም ካህን የሆነው የሙሴ ዐማት የትሮ፥ እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር መርቶ ባወጣቸው ጊዜ ለሙሴና ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገላቸውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ 2ስለዚህም በእርሱ ዘንድ ትቶአት ሄዶ የነበረችውን የሙሴን ሚስት ጺጳራን፥ #ዘፀ. 2፥21-22። 3እንዲሁም ከሙሴ የተወለዱትን ሁለቱን ልጆችዋን ይዞለት መጣ፤ ሙሴ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ጌርሾም ብሎ ጠራው፤ #ሐ.ሥ. 7፥29። 4እንዲሁም “የአባቴ አምላክ እግዚአብሔር ረዳኝ፤ በግብጽ ንጉሥም እጅ እንዳልገደል አዳነኝ” በማለት ሁለተኛውን ልጁን ኤሊዔዘር ብሎ ሰይሞት ነበር። #18፥4 ኤሊዔዘር፦ በዕብራይስጥ “እግዚአብሔር ረዳ” ማለት ነው። 5የትሮ የሙሴ ዐማት ከሙሴ ሚስትና ከሁለቱ ልጆችዋ ጋር ሆኖ በበረሓ ሙሴ ወደ ሰፈረበት ወደ ተቀደሰው ተራራ መጣ፤ 6መምጣታቸውንም ለማሳወቅ ለሙሴ መልእክት ልኮ ነበር፤ 7ስለዚህም ሙሴ ዐማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ራሱን ዝቅ አድርጎ እጅ በመንሣት ሳመው፤ ስለ ግል ጤንነታቸው ተጠያይቀው ወደ ሙሴ ድንኳን ገቡ፤ 8ሙሴም እስራኤልን ለመታደግ እግዚአብሔር በግብጽ ንጉሥና በሕዝቡም ላይ ያደረገውን ድንቅ ነገር ሁሉ ለዐማቱ ተረከለት። እንዲሁም ሕዝቡ በመንገድ ላይ ሳሉ ምን ያኽል ብርቱ ፈተና እንደ ገጠማቸውና እግዚአብሔርም እንዴት እንዳዳናቸው ነገረው። 9የትሮም ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ እግዚአብሔር ከግብጻውያን እጅ እስራኤልን ለማዳን ስላደረጋቸው መልካም ነገሮች ደስ ተሰኘ። 10እንዲህም አለ፥ “ከግብጽ ንጉሥና ከሕዝቡም እጅ ያዳናችሁ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! ሕዝቡንም ከባርነት ነጻ ያወጣ እግዚአብሔር ይመስገን! 11ግብጻውያን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ታብየው ያን ያኽል አሳፋሪ ድርጊት በመፈጸማቸው ይህን ሁሉ አስደናቂ ነገር ስላደረገ እነሆ፥ እኔም እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ የሚበልጥ መሆኑን አሁን ዐወቅሁ።” 12ከዚህም በኋላ የትሮ የሙሴ ዐማት በሙሉ የሚቃጠል ቊርባንና ሌላም ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት አመጣ፤ አሮንና የእስራኤል አለቆችም ሁሉ የተቀደሰውን ምግብ በአምልኮት ሥርዓት በእግዚአብሔር ፊት ለመመገብ ከሙሴ ዐማት ጋር መጡ።
የዳኞች መሾም
(ዘዳ. 1፥9-18)
13በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን በዳኝነት ለማገልገል ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በዙሪያው በመቆም አጨናንቀውት ከጠዋት እስከ ማታ ቈየ። 14የሙሴ ዐማት የትሮም ለሕዝቡ ያደርገው የነበረውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ ሲል ጠየቀው “ይህ ሁሉ ለሕዝቡ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው? ሕዝቡ አንተን ለማነጋገር በመፈለግ ከጠዋት እስከ ማታ በዙሪያህ በመቆም እንደዚህ የሚያጨናንቅህና አንተም ይህን ሁሉ ጉዳይ በዳኝነት ለማየት ብቻህን የምትቀመጠው ለምንድነው?”
15ሙሴም ለዐማቱ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ይህን ሁሉ የማደርግበት ምክንያት ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ወደ እኔ ስለሚመጣ ነው፤ 16ሁለት ሰዎች ተጣልተውም ወደ እኔ ቢመጡ የትኛው ወገን ትክክል እንደሆን ለማሳወቅ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት እነግራቸዋለሁ።”
17ከዚህም በኋላ የትሮ እንዲህ አለ፦ “ይህ የምታደርገው ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም፤ 18አንተን ራስህንም ሆነ ሕዝቡን በከንቱ ታደክማለህ፤ ብቻህን ሆነህ ይህን ሁሉ ለመሥራት ይከብድብሃል፤ 19እነሆ፥ እኔ አንድ ነገር ልምከርህ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ ሕዝቡን ወክለህ በእግዚአብሔር ፊት ጉዳያቸውን አቅርብ፤ 20አንተ የእግዚአብሔርን ሥርዓትና ሕግ ልታስተምራቸው፥ እንዲሁም እንዴት መኖርና ምን ማድረግ እንደሚገባቸውም ልትገልጥላቸው ይገባል፤ 21በተጨማሪ ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መርጠህ በሕዝቡ ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የኀምሳ አለቆችና የዐሥር አለቆች አድርገህ ሹም። እነርሱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፥ እምነት የሚጣልባቸውና በጉቦም የማይደለሉ ሰዎች መሆን አለባቸው። 22እነርሱ ሁልጊዜ ተገኝተው ከባድ ያልሆኑ ጉዳዮችን በማየት በዳኝነት ሕዝቡን ያገልግሉ፤ ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ከባድ ጉዳይ ወደ አንተ ያምጡት፤ እነርሱ በዚህ ዐይነት ሸክምህን ቢካፈሉልህ ሥራው ይቀልልሃል። 23በዚህ ዐይነት ብትሠራና ይህም የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆን ራስህን በከንቱ አታደክምም፤ ሕዝቡም በቀላሉ ጉዳዩ እየተፈጸመለት ወደየቤቱ ይሄዳል።”
24ሙሴም የዐማቱን ምክር ሁሉ ተቀብሎ በሥራ ላይ አዋለው። 25ከእስራኤላውያንም ሁሉ መካከል ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠ፤ እነርሱንም የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የኀምሳ አለቆችና የዐሥር አለቆች አድርጎ በሕዝቡ ላይ ሾማቸው። 26እነርሱም ከባድ ያልሆኑ ጉዳዮችን በማየት ሕዝቡን ሁልጊዜ በዳኝነት ያገለግሉ ጀመር፤ አስቸጋሪ የሆኑትን ጉዳዮች ብቻ ወደ ሙሴ ሲያቀርቡ፥ ቀላል የሆነውን ጠብና ክርክር ሁሉ ራሳቸው ይወስኑ ነበር።
27ሙሴም ዐማቱን በሰላም አሰናብቶት፤ ወደ አገሩ ተመለሰ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 18: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997