የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 2

2
የሙሴ መወለድ
1በዚያን ጊዜ ከሌዊ ነገድ የሆነ አንድ ሰው አንዲት ሌዋዊት ሴት አገባ፤ 2እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ሕፃኑ መልከ መልካም መሆኑን አይታ ሦስት ወር ሸሸገችው። #ሐ.ሥ. 7፥20፤ ዕብ. 11፥23። 3ሆኖም ከዚያ በላይ ልትሸሽገው አለመቻልዋን በተረዳች ጊዜ፥ በሣጥን መልክ ከደንገል የተሠራ ቅርጫት አዘጋጀች፤ ውሃም እንዳያስገባ በቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አስገብታ ቅርጫቱን በወንዝ ዳር በሚገኝ ቀጤማ መካከል አስቀመጠችው። 4የሕፃኑም እኅት የሚደርስበትን ነገር ለማየት ራቅ ብላ ትጠባበቀው ነበር።
5በዚህ ጊዜ የንጉሡ ሴት ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ሴቶች አገልጋዮችዋም በወንዙ ዳር ይሄዱ ነበር፤ እርስዋም በቀጤማ መካከል የተቀመጠ አንድ ቅርጫት አየች፤ አገልጋይዋንም ልካ አስመጣችው። 6በከፈተችውም ጊዜ አንድ ሕፃን በውስጡ አገኘች፤ ሕፃኑም ያለቅስ ስለ ነበር አዘነችለትና “ይህ ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ ነው” አለች።
7በዚያን ጊዜ የሕፃኑ እኅት የንጉሡን ልጅ “ይህን ሕፃን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች አንዲት ሞግዚት ልጥራልሽን?” ስትል ጠየቀቻት።
8“አዎ፥ ሄደሽ ጥሪልኝ” ስላለቻት ልጅቱ ሄደች፤ የሕፃኑንም እናት ጠርታ አመጣች። 9የንጉሡ ልጅም ሴትዮይቱን “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝሽንም እከፍልሻለሁ” አለቻት፤ ስለዚህ ሴቲቱ ሕፃኑን ወስዳ ታጠባው ጀመር። 10ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ንጉሡ ልጅ አመጣችው፤ የእርስዋም ልጅ ተባለ። እርስዋም “ከውሃ ያወጣሁት ስለ ሆነ ስሙ ሙሴ ተብሎ ይጠራ” አለች። #2፥10 ሙሴ፦ በዕብራይስጥ “ማውጣት” ማለት ነው።
የሙሴ ወደ ምድያም መኰብለል
# ሐ.ሥ. 7፥21። 11ሙሴ ባደገ ጊዜ ወገኖቹን ለመጐብኘት ሄደ፤ ከባድ ሥራ መሥራታቸውን ተመለከተ፤ እንዲያውም አንድ ግብጻዊ ከወገኖቹ አንዱ የሆነውን ዕብራዊ ሲደበድብ አየ። #ዕብ. 11፥24። 12ሙሴ ዙሪያውን ተመልክቶ ማንም እንደማያየው ከተረዳ በኋላ ግብጻዊውን ገድሎ በአሸዋ ውስጥ ደበቀው። 13በማግስቱም ወደዚያው ስፍራ ተመልሶ ሲሄድ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ በደል የሠራውንም ሰው ተመልክቶ “ወገንህ የሆነውን ዕብራዊ ለምን ትመታዋለህ?” ሲል ጠየቀው። 14ሰውየውም “አንተን በእኛ ላይ ገዢና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ወይስ ያንን ግብጻዊ እንደ ገደልክ እኔንም መግደል ትፈልጋለህን?” አለው፤ ሙሴም እጅግ ፈርቶ “ያደረግኹት ነገር ታውቋል ማለት ነው” ብሎ አሰበ። #ሐ.ሥ. 7፥23-28። 15ንጉሡም የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ሙሴን ለማስገደል ፈለገ፤ ሙሴ ግን ኰብልሎ በዚያው ለመኖር ወደ ምድያም አገር ሄደ። #ሐ.ሥ. 7፥29፤ ዕብ. 11፥27።
እዚያም እንደ ደረሰ በውሃ ጒድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ 16አንድ የምድያም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ውሃ ለመቅዳትና በገንዳ እየሞሉ የአባታቸውን በጎችና ፍየሎች ለማጠጣት ወደዚያ መጡ። 17እረኞችም መጥተው እነዚያን ሴቶች አባረሩአቸው፤ ሙሴም ሴቶቹን ከእረኞቹ እጅ በማዳን መንጋቸውን ውሃ አጠጣላቸው። 18እነዚያም ሴቶች ልጆች ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤል በተመለሱ ጊዜ “ዛሬ እንዴት በፍጥነት ተመለሳችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። #2፥18 ራጉኤል፦ የሙሴ አማች ሲሆን ሌላ ስሙ “የትሮ” ነው።
19እነርሱም “አንድ ግብጻዊ ከእረኞች እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውሃ እየቀዳ መንጋችንን አጠጣልን” ብለው መለሱለት። 20አባታቸውም “ታዲያ፥ አሁን ሰውየው የት ነው? ለምንስ ተዋችሁት? ሂዱ ጥሩትና መጥቶ እህል ይቅመስ” አላቸው።
21ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ለመኖር ፈቃደኛ ሆነ፤ ያም ሰው ልጁን ጺጳራን ሚስት ትሆነው ዘንድ ለሙሴ ሰጠው። 22እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ሙሴም “እኔ በዚህ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ልጁን ጌርሾም ብሎ ጠራው። #2፥22 ጌርሾም፦ በዕብራይስጥ “መጻተኛ” ማለት ነው።
23ከብዙ ዓመቶች በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያን ግን አሁንም በባርነት ቀንበር ሥር በመጨነቅ ርዳታ ለማግኘት በመጮኽ ላይ ነበሩ፤ ጩኸታቸውም ወደ እግዚአብሔር ደረሰ። 24ጭንቀት የተሞላበትን ጩኸታቸውንም ሰምቶ እግዚአብሔር ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አስታወሰ። #ዘፍ. 15፥13-14። 25እግዚአብሔር እስራኤላውያን በባርነት መጨነቃቸውን አይቶ ስለ እነርሱ አሰበ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ