የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 25

25
ለቤተ እግዚአብሔር የሚቀርብ ስጦታ
(ዘፀ. 35፥4-9)
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“ስጦታን ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤላውያን ንገር፤ ማንኛውም ሰው በፈቃዱ የሚያመጣውን መባ ሁሉ ተቀበል። 3የስጦታውም ዐይነት ይህ ነው፦ ወርቅ፥ ብር፥ ነሐስ፥ 4ሰማያዊና ሐምራዊ፥ ቀይም ከፈይ፥ ጥሩ በፍታ፥ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ልብስ፥ 5ተለፍቶ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፤ የተለፋ የፍየል ቆዳ፥ የግራር እንጨት፥ 6ለመብራት የሚሆን የወይራ ዘይት፥ ለቅባት ዘይትና ለዕጣን ሽታ የሚሆን ቅመማ ቅመም፥ 7መረግድ፥ (ቅጠልያ ዕንቊ) በሊቀ ካህናቱ ኤፉድና በደረት ኪስ ላይ የሚደረግ ፈርጥ፥ 8በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ሕዝቡ ቤተ መቅደስ ይሥሩልኝ፤ 9ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ እኔ በማሳይህ ዕቅድ መሠረት ሥሩት።
የቃል ኪዳኑ ታቦት
(ዘፀ. 37፥1-9)
10“ከግራር እንጨት የተሠራ አንድ ሣጥን፥ ታቦት አድርገው ይሥሩ፤ ርዝመቱ መቶ ዐሥር የጐኑ ስፋት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱም ስድሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ይሁን፤ 11ውስጡንም ውጪውንም በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አብጅለት፤ 12አራት የወርቅ ዋልታዎችንም ሠርተህ ሁለቱን በአንድ በኩል፥ ሁለቱንም በሌላ በኩል በማድረግ ከአራቱም እግሮቹ ጋር እንዲያጣብቁ አድርግ፤ 13ለታቦቱ መሸከሚያ የሚሆኑ መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፤ በወርቅም ለብጣቸው፤ 14እነዚህንም መሎጊያዎች በታቦቱ አራት ማእዘን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባ። 15መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፤ ከቶም ከዚያ አይውጡ። 16ከዚህም በኋላ እኔ የምሰጥህን፥ ትእዛዞቹ የተጻፉባቸውን ሁለት ጽላቶች በታቦቱ ውስጥ አኑር።
17“ርዝመቱ መቶ ኻያ አምስት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሰባ አምስት ሳንቲ ሜትር የሆነም የስርየት መክደኛ ሥራለት። #25፥17 የስርየት መክደኛ፦ ለታቦቱ መክደኛ የተሰጠ ስም ነው። #ዕብ. 9፥5። 18ከተቀጠቀጠም ወርቅ ክንፎች ያሉአቸው የሁለት ኪሩቤል ምስል ሥራ፤ 19በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት በኩል በጫፍና በጫፍ አኑራቸው፤ እነርሱም ከክዳኑ ጋር አብረው የተሠሩ ይሁኑ። 20እነዚህም ክንፍ ያላቸው ኪሩቤል በመክደኛው ግራና ቀኝ ሆነው ፊት ለፊት የሚተያዩ ይሁኑ፤ በተዘረጉትም ክንፎቻቸው መክደኛውን ይሸፍኑት። 21በታቦቱ ላይ መክደኛውን አድርግ፤ የምሰጥህንም ጽላት በታቦቱ ውስጥ አኑረው፤ 22እኔም በዚያ ለአንተ እገለጥልሃለሁ፤ በመክደኛው ላይ በተሠሩት ክንፍ ባላቸው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል ሆኜ ለእስራኤል ሕዝብ የምታቀርበውን ትእዛዞቼን ሁሉ እሰጥሃለሁ።
ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ ጠረጴዛ
(ዘፀ. 37፥10-16)
23“ርዝመቱ ሰማኒያ ስምንት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑ ስፋት አርባ አራት ሳንቲ ሜትር፥ ከፍታውም ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር የሆነ ጠረጴዛ ከግራር እንጨት ሥራ። 24በንጹሕ ወርቅም ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አድርግለት። 25በዙሪያው ሰባ አምስት ሳንቲ ሜትር ስፋት የሚሆን ጠርዝ አብጅለት፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ አድርግለት። #ዘሌ. 24፥5-8። 26ከወርቅ የተሠሩ አራት መሸከሚያ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም እግሮቹ ባሉበት በአራቱም ማእዘን አኑራቸው። 27ጠረጴዛውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ የሚሰኩባቸው ቀለበቶች ከክፈፉ ጋር የተቀራረቡ ይሁኑ። 28መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 29ሳሕኖችንና ጭልፋዎችን እንዲሁም ለወይን ጠጅ መቅጃ የሚሆኑ ማንቆርቆሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ከንጹሕ ወርቅ ሥራ። 30ጠረጴዛውም በታቦቱ ፊት ለፊት ይቀመጥ፤ ለእኔ የሚቀርበው የተቀደሰ ኅብስት ዘወትር በጠረጴዛው ላይ መኖር አለበት።
የመብራቱ መቅረዝ
(ዘፀ. 37፥17-24)
31“ከንጹሕም ወርቅ መቅረዝ ሥራ፤ የመቅረዙን መሠረትና ዘንግ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፤ ለጌጥ የሚሠሩት የአበባዎች ወርድ እንቡጦችና ቀንበጦች ጨምሮ ከእርሱ ጋር አንድ ሆነው ይሠሩ። 32በስተጐኑ ስድስት ቅርንጫፎች አውጣለት፤ ይኸውም ሦስቱ በአንድ ጐን ሲሆኑ፥ ሦስቱ ደግሞ በሌላ ጐን ይሁኑ። 33ስድስቱም ቅርንጫፎች እያንዳንዳቸው እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስል ሦስት የአበባ ወርድ ጌጥ ይኑራቸው። 34የመቅረዙም ዘንግ እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስል አራት የአበባ ወርድ ጌጥ ያለው ይሁን። 35ከሦስቱ ጥንድ ቅርንጫፎች በእያንዳንዱ ጥንድ ሥር አንድ እንቡጥ ይኑር። 36እንቡጦቹ፥ ቅርንጫፎቹና መቅረዙ ሁሉም አንድ ወጥ ሆነው ከንጹሕ ወርቅ ተቀርጸው ይሠሩ። 37ለመቅረዙም ሰባት መብራቶች ሠርተህ ከፊት ለፊት በኩል እንዲያበሩ፥ ከፍ አድርገህ አስቀምጣቸው። 38መኰስተሪያዎችንና የኲስታሪ ማስቀመጫ ሳሕኖችን ከንጹሕ ወርቅ ሥራ፤ 39መቅረዙንና እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች የምትሠራበት ሠላሳ አምስት ኪሎ ግራም ንጹሕ ወርቅ ይሁን። 40በተራራው ላይ ባሳየሁህ ዕቅድ መሠረት ለመሥራት ጥንቃቄ አድርግ። #ሐ.ሥ. 7፥44፤ ዕብ. 8፥5።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ