ኦሪት ዘጸአት 27
27
የመሠዊያው አሠራር
(ዘፀ. 38፥1-7)
1“ከግራር እንጨት መሠዊያ ሥራ፤ ርዝመቱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የጐኑ ስፋት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ቁመቱም አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ይሁን። 2በአራቱም ማእዘን ጫፍ ላይ ጠርበህ ቀንድ መሳይ ጒጦች አውጣ፤ ይህም ከመሠዊያው ጋር አብሮ የተሠራ ይሁን፤ እርሱም በነሐስ የተለበጠ ይሁን። 3ዐመድ የሚጠራቀምባቸውን ድስቶችን፥ የእሳት መጫሪያዎችን፥ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፥ ሜንጦዎችንና ማንደጃዎችን አዘጋጅ፤ ሁሉም ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ። 4እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የነሐስ መከላከያ አብጅለት፤ ለመከላከያውም አራት የነሐስ ቀለበቶች በአራቱም ማእዘን አድርግለት። 5መከላከያም እስከ መሠዊያው እኩሌታ እንዲደርስ ከመሠዊያው ክፈፍ በታች አድርገው፤ 6ለመሠዊያው መሸከሚያ የሚሆኑ መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በነሐስ ለብጣቸው። 7መሠዊያውን መሸከም በሚያስፈልግበትም ጊዜ መሎጊያዎቹን ከመሠዊያው በእያንዳንዱ ጐን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አግባ። 8በተራራው ላይ ባሳየሁህ ዕቅድ መሠረት መሠዊያውን ከሳንቃዎች ሥራ፤ ውስጡም ባዶ ይሁን።
የድንኳኑ አደባባይ ክልል
(ዘፀ. 38፥9-20)
9“ለድንኳኑ አደባባይ ክልል መጋረጃዎች ከቀጭን ሐር ሥራ፤ የመጋረጃዎቹም ርዝመት ከደቡብ በኩል አርባ አራት ሜትር ይሁን፤ 10ለእርሱም መደገፊያ ኻያ የነሐስ እግሮች ያላቸው ኻያ ምሰሶዎች ሥራ፤ በእነርሱም ላይ ከብር የተሠሩ ዘንጎችና ኩላቦች ይኑሩ፤ 11በስተ ሰሜን በኩል ላለውም አደባባይ ልክ በዚሁ ዐይነት ይሠራ። 12በምዕራብ በኩል አደባባይ ዐሥር እግሮች ካሉአቸው ዐሥር ምሰሶዎች ጋር ርዝመታቸው ኻያ ሁለት ሜትር የሚሆን መጋረጃዎች ይኑሩት። 13የመግቢያው በር ባለበት በምሥራቅ በኩል የአደባባዩ ስፋት ኻያ ሁለት ሜትር ይሁን። 14በበሩ በአንድ በኩል ያለው መጋረጃ ስድስት ሜትር ከስድሳ ሳንቲ ሜትር ሲሆን ሦስት ምሰሶዎች ከሦስት እግር ጋር ይሁኑ። 15በሌላው በኩል ያለውም መጋረጃ እንደዚሁ ይሁን። 16ለአደባባዩ በር ርዝመታቸው ዘጠኝ ሜትር የሆነ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ የተሠራ በጥልፍ ያጌጠ መጋረጃ ይኑረው፤ የሚደግፉትም አራት እግሮች ያሉአቸው አራት ምሰሶዎች ይኑሩት። 17በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት ምሰሶዎች ሁሉ በብር ዘንጎች ይያያዙ፤ ኲላቦቻቸው ከብር፥ እግሮቻቸውም ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ። 18የድንኳኑ አደባባይ ርዝመቱ አርባ አራት ሜትር የጐኑ ስፋት ኻያ ሁለት ሜትር፥ ከፍታውም ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ይሁን፤ መጋረጃዎቹ ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ሆነው የነሐስ እግሮች ይኑሩአቸው። 19በድንኳኑ ውስጥ የሚገኙት ለማናቸውም ጥቅም የሚውሉ የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ የድንኳኑና የአደባባዩ ካስማዎች ሁሉ ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ።
ስለ መብራት የሚደረግ ጥንቃቄ
(ዘሌ. 24፥1-4)
20“መብራቱ በየምሽቱ ሲበራ እንዲኖር ለመብራት የሚሆነውን ተጨምቆ የተጠለለ ምርጥ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ሕዝብ እዘዝ፤ 21አሮንና ልጆቹ ከምሽት እስከ ንጋት ይበራ ዘንድ የእግዚአብሔር መገኛ ከሆነው ፊት ከቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ካለው መጋረጃ ውጪ ያኑሩት፤ ይህም በእስራኤል ሕዝብና ወደፊትም በሚነሣው ትውልድ ዘንድ ቋሚ ሥርዓት ሆኖ ይኑር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 27: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997