የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 16

16
እምነት የጐደላት ኢየሩሳሌም
1እግዚአብሔርም እንደገና እንዲህ አለኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ኢየሩሳሌም ያደረገችው ነገር ምን ያኽል አጸያፊ እንደ ሆነ አስታውቃት፤ 3ልዑል እግዚአብሔር ስለ እርስዋ የሚለውንም እንዲህ ብለህ ንገራት፦
“የተወለድሽው በከነዓን ምድር ነበር፤ አባትሽ አሞራዊ ሲሆን እናትሽም ሒታዊ ነበረች፤ 4በተወለድሽ ጊዜ እትብትሽን አልተቈረጠም፤ ንጹሕ ትሆኚ ዘንድ በውሃ አልታጠብሽም፥ ወይም በጨው ታሽተሽ በጨርቅ አልተጠቀለልሽም። 5ከነዚህ ነገሮች አንዱን እንኳ ለማድረግ ለአንቺ ርኅራኄ ያለው ማንም አልነበረም፤ ስትወለጂ የተጠላሽ ስለ ነበርሽ በሜዳ ላይ ተጣልሽ።
6“እኔም በዚያ ሳልፍ በገዛ ደምሽ ተነክረሽ ስትንፈራገጪ አገኘሁሽ፤ በደም ተሸፍነሽ ልትሞቺ ነበረ፤ በሕይወት እንድትኖሪ አደረግሁሽ። 7ምቾት እንዳለው ተክል እንድታድጊ አደረግሁ፤ ቁመትና ጠንካራ ሰውነት በመጨመር አድገሽ የተዋብሽ ወጣት ሆንሽ፤ ጡትሽ አጐጠጐጠ፤ ጠጒርሽ ረዘመ፤ ነገር ግን እርቃንሽን ነበርሽ።
8“እንደገናም በአጠገብሽ ሳልፍ ጊዜሽ የፍቅር ዕድሜ ነበር፤ የተራቈተውን ሰውነትሽንም በመጐናጸፊያዬ ሸፍኜ ቃል ገባሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር እንደ ጋብቻ ያለ ቃል ኪዳን ገብቼ የእኔ የግሌ አደረግሁሽ፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።
9“ከዚያም በኋላ መላ አከላትሽንና በደም የተበከለ ሰውነትሽን አጠብኩ፤ የወይራ ዘይትም ቀባሁሽ፤ 10ጥበብ ቀሚስ አለበስኩሽ፤ ከምርጥ ቆዳ የተሠራ ጫማ አደረግሁልሽ፤ ሐር ሻሽ በራስሽ ላይ አሰርኩልሽ፤ ውድ የሆነ ካባ ደረብኩልሽ። 11በጌጥ አስጌጥኩሽ፤ የእጅ አንባርና የአንገት ድሪ አደረግሁልሽ። 12ለአፍንጫሽ ቀለበት፥ ለጆሮሽ ጒትቻ፥ እንዲሁም በራስሽ ላይ የምትደፊው ውብ የሆነ አክሊል ሰጠሁሽ። 13ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ብዙ ጌጣጌጦች ነበሩሽ፤ ከልዩ ልዩ ሐር የተሠሩና በጥልፍ ጌጥ የተዋቡ ውድ ልብሶች ነበሩሽ፤ ምርጥ ከሆነ ዱቄት የተጋገረ ዳቦ፥ ማርና የወይራ ዘይት ትመገቢ ነበር፤ ውበትሽ እጅግ እየጨመረ ስለ ሄደ ንግሥት ለመሆን በቃሽ። 14ግርማ ሞገሴን በአንቺ ላይ አሳርፌ የተዋብሽ ስላደረግሁሽ እንከን ከሌለበት ቊንጅናሽ የተነሣ በሁሉ አገር ታወቅሽ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።
15“ነገር ግን በውበትሽና በዝናሽ ተማምነሽ ከዐላፊ አግዳሚ ሁሉ ጋር የዝሙት ሥራ ፈጸምሽ። 16ከልብሶችሽ ጥቂቱን ወስደሽ የመስገጃ ስፍራዎችሽን አስጌጥሽባቸው፤ በዚያም አመንዝራነትሽን ቀጠልሽ፤ እነዚህ ድርጊቶች መፈጸም አልነበረባቸውም፤ ከቶም መፈጸም አይገባቸውም፤ 17እኔ የሰጠሁሽን ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ጌጣጌጦችን ወስደሽ የወንድ ጣዖቶችን በመሥራት ከእነርሱ ጋር አመነዘርሽ። 18እኔ የሰጠሁሽንም በጥልፍ ያጌጡ ልብሶችሽንም ወስደሽ ምስሎቹን አለበስሽ፤ እኔ የሰጠሁሽንም የወይራ ዘይትና ዕጣን ለምስሎቹ አቀረብሽ። 19ምርጥ የሆነ ዱቄት የወይራ ዘይትና ማር. ምግብ እንዲሆንሽ ሰጥቼሽ ነበር፤ አንቺ ግን ጣዖቶችን ለማስደሰት መልካም መዓዛ ያለው መሥዋዕት አድርገሽ አቀረብሽ፤” ይህም ተደርጓል፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
20“ዝሙት መሥራትሽ አልበቃ ብሎሽ የወለድሽልኝንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወስደሽ ለጣዖቶች መሥዋዕት በማድረግ አቀረብሻቸው። 21ልጆቼን በማረድ ለጣዖቶች መሥዋዕት አድርገሽ አቀረብሽ። 22እጅግ አጸያፊ በሆነ የአመንዝራነት ኑሮሽ የልጅነትሽን ሁኔታ አላስታወስሽውም፤ ይህም ማለት ራቁትሽን በደም ተነክረሽ ስትንፈራገጪ የነበርሽበት ጊዜ ፈጽሞ ትዝ አላለሽም።”
በኢየሩሳሌም ላይ የተሰነዘረ ወቀሳ
23ልዑል እግዚአብሔር “ወዮልሽ! ወዮልሽ!” ይላል። ያን ሁሉ ክፉ ነገር ከፈጸምሽ በኋላ 24መድረክ እየሠራሽ በየ አደባባዩ ለራስሽ ከፍ ያለ ቦታ አዘጋጀሽ። 25በዚህ ዐይነት በየአውራ መንገዱ ዳር የጣዖት ማምለኪያ ቦታዎችን ሠርተሽ ውበትሽን አረከስሽ፤ ለመጣው ሁሉ ሰውነትሽን አሳልፈሽ እየሰጠሽ በየቀኑ አመንዝራነትሽን አበዛሽ። 26እነዚያ ቅንዝረኞች የሆኑ ግብጻውያን ጐረቤቶችሽ ከአንቺ ጋር የዝሙት ሥራ እንዲፈጽሙ አደረግሽ፤ እኔን ለማስቈጣት ምንዝርናሽን አበዛሽ።
27“አሁን ግን አንቺን ለመቅጣትና ድርሻሽ የሆነውንም በረከት ከአንቺ ለመቀነስ እጄን ዘርግቼአለሁ፤ እነርሱ የፈለጉትን እንዲያደርጉ አንቺን ለጠላቶችሽ፥ ብልግናሽ ለሚያስደነግጣቸው ለፍልስጥኤማውያን አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ።
28“ከሌሎች ጋር የምትፈጽሚው የዝሙት ሥራ አልበቃ ብሎሽ ከአሦራውያን ጋር አመነዘርሽ፤ ነገር ግን እነርሱም አላረኩሽም፤ 29ነጋዴዎች ለሆኑት ባቢሎናውያንም ወዳጅ ሆነሽ ታመነዝሪ ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም አላረኩሽም።”
30ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ኀፍረተቢስ እንደ ሆነች አመንዝራ ሴት ይህን ሁሉ ማድረግሽ እንዴት መንፈሰ ደካማ ብትሆኚ ነው? 31በየመንገዱ ዳር መድረክሽን ትሠሪአለሽ፤ በየአደባባዩም የጣዖት ማምለኪያ ቦታሽን ታዘጋጂአለሽ፤ ሆኖም እንደ ተራ አመንዝራ ሴት ገንዘብ ለመሰብሰብ እንኳ አልፈለግሽም። 32አንቺ፥ ዘማዊት ሚስት! ባልዋን ማፍቀር ትታ ከባዕዳን ጋር እንደምታመነዝር ሴት ሆንሽ። 33አመንዝራ ሴት ገንዘብ ይከፈላት ነበር፤ አንቺ ግን ገንዘብ በመቀበል ፈንታ ለወዳጆችሽ ስጦታ ታበረክቺአለሽ፤ ከየአቅጣጫው መጥተው ከአንቺ ጋር ያመነዝሩ ዘንድ መደለያ ገንዘብ ሰጠሽ። 34ስለዚህም አንቺ ልዩ ዐይነት አመንዝራ ሴት ሆነሻል። ነገር ግን እንደዚህ እንድትሆኚ ያባበለሽ የለም፤ ገንዘብ ትከፍያቸዋለሽ እንጂ የሚከፍልሽ የለም፤ ስለዚህ በእርግጥ በአመንዝራነትሽ አንቺ ልዩ ነሽ።”
የእግዚአብሔር ፍርድ በኢየሩሳሌም ላይ
35አንቺ አመንዝራ ኢየሩሳሌም! እግዚአብሔር የሚለውን ስሚ! 36ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በፍትወትሽ ተቃጥለሻል፤ ለፍቅረኞችሽ ገላሽን አጋልጠሽ ሰጥተሻል፤ አጸያፊ ጣዖቶችን ሁሉ አምልከሻል፤ የልጆችሽንም ደም አፍስሰሽ ለጣዖቶቹ መሥዋዕት አቅርበሻል። 37በዚህ ምክንያት ከእነርሱ ጋር የተደሰትሽባቸውን ማለት የወደድሻቸውንና የጠላሻቸውን ሁሉ ተጋልጠሽ ዕርቃንሽን ያዩ ዘንድ ከአካባቢው ሰብስቤ አንቺን በፊታቸው አራቊትሻለሁ። 38እኔ በአንቺ ላይ፥ ዝሙት በፈጸሙና ሕይወት ባጠፉ ሴቶች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፤ አንቺን በቅናቴና በቊጣዬ አጠፋሻለሁ። 39በሥልጣናቸው ሥር እንድትሆኚ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም መድረክሽንና ከፍተኛ ቦታዎችሽን ያፈራርሳሉ፤ ልብስሽን ገፈው ጌጣጌጥሽንም ወስደው ያራቊቱሻል፤ ባዶ እጅሽንም ያስቀሩሻል።
40“በድንጋይ ወግሮ፥ በሰይፍ ቈራርጦ የሚገድልሽን ሕዝብ በአንቺ ላይ እያነሣሡ ናቸው፤ 41ቤቶችሽን በእሳት ያቃጥላሉ፤ በብዙ ሴቶች ፊት ፍርድን ተግባራዊ ያደርጉብሻል፤ በዚህ ዐይነት አመንዝራነትሽንና ለወዳጆችሽ የዝሙት ዋጋ መክፈልሽን እንድትተዪ አደርግሻለሁ። 42ስለዚህ በአንቺ ላይ ያለኝ ቊጣ ያበቃል፤ ቅናቴም ከአንቺ ይርቃል፤ በአንቺ ላይ የነበረው ቊጣዬም ይበርዳል፤ ዳግመኛም አልቈጣም። 43በልጅነትሽ ወራት ያደረግኹልሽን ሁሉ ረሳሽ፤ በፈጸምሽውም ክፉ ሥራ አስቈጣሽኝ፤ ስለዚህ እኔም በሠራሽው ኃጢአት መጠን ዋጋሽን እንድትቀበይ አደረግሁ፤ በፈጸምሽው አጸያፊ ሥራ ሁሉ ላይ የዝሙትን ርኲሰት መጨመርሽ ለምን ይሆን?” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።
ልጅትዋም እንደ እናትዋ
44እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ኢየሩሳሌም ሆይ! ሰዎች ስለ አንቺ ‘ልጅትዋም እንደ እናትዋ ሆነች!’ እያሉ መተረቻ ያደርጉሻል። 45በእርግጥም አንቺ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ እናትሽ ባልዋንና ልጆችዋን ጠልታ ነበር፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንደ ጠሉ እንደ እኅቶችሽ ነሽ፤ አንቺና እኅቶችሽ ሒታዊ እናትና አሞራዊ አባት ነበራችሁ።
46“ታላቅ እኅትሽ ከመንደሮችዋ ጋር በስተ ሰሜን የምትገኘው ሰማርያ ናት፤ ታናሽ እኅትሽም ከመንደሮችዋ ጋር በስተ ደቡብ የምትገኘው ሰዶም ናት፤ 47የእነርሱን አካሄድ ተከትለሽ አጸያፊ ሥራቸውን መሥራትሽ ብቻ ሳይሆን በአካሄድሽ ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእነርሱ የበለጠ ጥፋት ሠራሽ።
48“እኔ ሕያው እንደ መሆኔ የምለው ይህ ነው፤ እኅትሽ ሰዶምና መንደሮችዋ አንቺና መንደሮችሽ ካደረጋችሁት የባሰ ክፋት አልሠሩም፤” ይላል ልዑል እግዚአብሔር። 49የእኅትሽ የሰዶም በደል ይህ ነው፤ እርስዋና መንደሮችዋ ኲራት ተሰምቶአቸው ነበር። የተትረፈረፈ ምግብና የተዝናና ኑሮ ቢኖራቸውም ችግረኞችንና ድኾችን አይረዱም ነበር። 50እነርሱ ትዕቢተኞች በመሆን እኔ የምጠላውን ነገር ሁሉ ፈጸሙ፤ አንቺም እንደምታውቂው ደመሰስኳቸው።
51“ሰማርያም ብትሆን የአንቺን ግማሽ ያኽል እንኳ ኃጢአት አልሠራችም፤ ከእርስዋ ይበልጥ አንቺ እጅግ አጸያፊ የሆነ ኃጢአት ሠርተሻል። የአንቺ ርኲሰት ከእኅቶችሽ ጋር ቢመዛዘን እነርሱን ከበደል ነጻ ያስመስላቸዋል። 52እነሆ አሁንም ውርደትሽን ተሸከሚ፤ የአንቺ ኃጢአት እጅግ የከፋ ከመሆኑ የተነሣ እኅቶችሽ ከአንቺ ጋር ሲነጻጸሩ ምንም በደል የሌለባቸው ንጹሖች መስለው ይታያሉ፤ አሁንም እኅቶችሽን በደል የሌለባቸው ንጹሖች እንዲመስሉ በማድረግሽ ኀፍረትን እንደ ልብስ ተከናንበሽ ተቀመጪ።”
የሰዶምና የሰማርያ መታደስ
53እግዚአብሔር ስለ ኢየሩሳሌም እንዲህ አለ፦ “ለሰዶምና ለመንደሮችዋ፥ ለሰማርያና መንደሮችዋ የቀድሞ ሀብታቸውን እንደምመልስ የአንቺንም ሀብት እመልስልሻለሁ። 54አንቺም ውርደትሽን ተከናንበሽ ባደረግሽው ነገር ሁሉ ታፍሪአለሽ። ሰዶምና ሰማርያ ይህን ሁናቴሽን በሚያዩበት ጊዜ ያንቺን ያኽል ኃጢአተኞች ባለመሆናቸው ይጽናናሉ። 55እኅቶችሽን በተመለከተ ግን ሰዶምና መንደሮችዋ ሰማርያና መንደሮችዋ ወደ ቀድሞ ሁናቴአቸው ይመለሳሉ፤ እንዲሁም አንቺና መንደሮችሽ ወደ ቀድሞ ሁናቴአችሁ ትመለሳላችሁ። 56ዕብሪተኛ በነበርሽበት ዘመን እኅትሽ ሰዶም የአንቺ መሳለቂያ አልነበረችምን? 57ይህንንስ ያደረግሽው የአንቺ በደል ከመታወቁ በፊት አይደለምን? አሁን ግን አንቺ ለሶርያ ከተሞችና ለጐረቤቶቻቸው እንዲሁም ለፍልስጥኤም ከተሞችና ባካባቢው ላሉ ለሚንቁሽ ሁሉ መሳለቂያ ሆነሻል። 58በስድነትሽ በአጸያፊ ተግባርሽ ቅጣትሽን መቀበል አለብሽ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
ለዘለዓለም የሚጸና ቃል ኪዳን
59ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሰጠሽውን የተስፋ ቃል ንቀሽ ቃል ኪዳን በማፍረስሽ የሚገባሽን ቅጣት እሰጥሻለሁ። 60ነገር ግን በወጣትነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ። ከአንቺ ጋርም የዘለዓለሙን ቃል ኪዳን አጸናለሁ። 61ታላቅና ታናሽ እኅቶችሽን ወስጄ ለአንቺ እንደ ልጆችሽ አድርጌ በምሰጥበት ጊዜ የቀድሞውን አካሄድሽን አስታውሰሽ ታፍሪአለሽ። ይህ የሚሆነው ግን ከአንቺ ጋር በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት አይደለም። 62ከአንቺ ጋር ቃል ኪዳኔን አድሳለሁ። አንቺም በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቂያለሽ፤ 63ይህንንም የማደርገው፥ ለፈጸምሽው በደል ሁሉ ይቅርታ ሳደርግልሽ ሥራሽን በማስታወስ በድንጋጤ ዐፍረሽ ጸጥ እንድትዪ ነው፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ