ትንቢተ ሕዝቅኤል 23
23
በዝሙት ኃጢአት የተባበሩ እኅትማማች
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ከአንድ እናት የሚወለዱ ሁለት እኅትማማች ነበሩ፤ 3እነርሱም በወጣትነታቸው ወራት በግብጽ ሲኖሩ ክብርናቸውን አጥተው በመዋረድ አመንዝሮች ሆኑ። 4ከእነርሱም ታላቂቱ ኦሆላ ትባል ነበር፤ እርስዋም ሰማርያ ነች፤ ታናሽቱ ደግሞ ኦሆሊባ ትባል ነበር እርስዋም ኢየሩሳሌም ነች፤ እኔ ሁለቱንም አግብቼ ልጆች ወለዱልኝ። 5ኦሆላ እኔ ካገባኋት በኋላ እንኳ አመንዝራነትዋን ቀጠለች፤ በአሦራውያን ወዳጆችዋም ፍቅር ተቃጠለች። 6እነርሱም ሐምራዊ የለበሱ ታላላቅ መሳፍንት፥ ከፍተኛ ማዕርግ ያላቸው መኰንኖች ነበሩ፤ ሁሉም ወጣትነት ያላቸውና መልከ ቀና የሆኑ ፈረሰኞች ነበሩ። 7እርስዋም ለአሦራውያን ባለ ሥልጣኖች ሁሉ መጠቀሚያ አመንዝራ ነበረች፤ ፍትወትዋም የአሦራውያንን ጣዖቶች በማምለክ ራስዋን እንድታረክስ አደረጋት። 8ክብርናዋን ባጣችበት በግብጽ የጀመረችውን አመንዝራነት ቀጥላለች፤ ከልጃገረድነትዋ ጊዜ ጀምሮ ወንዶች ሁሉ እርስዋን እንደ አመንዝራ በመቊጠር ከእርስዋ ጋር ያመነዝራሉ። 9ስለዚህ እጅግ ለምትፈልጋቸው ለአሦራውያን ወዳጆችዋ አሳልፌ ሰጠኋት፤ 10እነርሱም ልብስዋን ገፈው እርቃንዋን አስቀሩአት፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋን በምርኮ ያዙ፤ እርስዋንም በሰይፍ ገደሉአት፤ ፍርድም በእርስዋ ላይ ተግባራዊ ሆነ፤ ሴቶች ሁሉ ስለ ገጠማት መጥፎ ዕድል አሉባልታ ማሰማት ጀመሩ።
11“እኅትዋ ኦሆሊባ ይህንንም ካየች በኋላ ባሰባት እንጂ አልታረመችም፤ እንዲያውም ከኦሆላ የበለጠ አመንዝራ ሆነች። 12እርስዋም በበኩልዋ ታላላቅ የአሦራውያን መሳፍንትንና የጦር መኰንኖችን፥ ደማቅ ልብስ የሚለብሱ ወታደሮችንና መልከቀና የሆኑ ወጣትነት ያላቸውን ፈረሰኞች በማፍቀር በፍትወት የተቃጠለች ሆነች። 13ይህችም ሁለተኛይቱ ረከሰች፤ ሁለቱም በአንድ ዐይነት መንገድ ተጓዙ።
14-15“አመንዝራነትዋም እየባሰ ሄደ፤ በወገቦቻቸው ዙሪያ የሚያማምሩ ቀለበቶችን ታጥቀው፥ በራሶቻቸውም ላይ ጌጠኛ ጥምጥም ጠምጥመው፥ በደማቅ ሐምራዊ ቀለም በግድግዳ ላይ የተቀረጹትን ከፍተኞች የሆኑት ባለሥልጣኖችን ምስሎች አይታ ተማረከች። 16ልክ እነርሱን ስታይ በፍትወት ተቃጥላ እነርሱ ወደሚኖሩባት ወደ ባቢሎን መልእክተኞችን ላከች፤ 17ባቢሎናውያንም ከእርስዋ ጋር ለማመንዘር መጡ፤ ብዙ ጊዜ ስላረከሱአት በመጨረሻ ሁሉንም በመጸየፍ ጠላቻቸው። 18እርቃንዋን ወደ አደባባይ በመውጣት አመንዝራነትዋ በሰው ሁሉ ዘንድ እንዲጋለጥ አደረገች፤ እኔም እኅትዋን የተጸየፍኩትን ያኽል እርስዋንም ተጸየፍኳት። 19እርስዋም በልጃገረድነትዋ ወራት በግብጽ አመንዝራ ሆና ሳለ ስታደርግ የነበረውን ሁሉ በመፈጸም አመንዝራነትዋን አበዛች። 20ብልቶቻቸው እንደ አህያ፥ ዘራቸውም እንደ አለሌ ፈረስ ሆኖ በፍትወት በሚቃጠሉ ወንዶች ተማረከች። 21ኦሆሊባ ሆይ! በልጃገረድነትሽ ወራት ወንዶች በጡቶችሽ እየተጫወቱ ክብረ ንጽሕናሽን ባጣሽ ጊዜ ትፈጽሚው የነበረውን ርኲሰት ደግመሽ መፈጸም ትፈልጊያለሽ።
እግዚአብሔር በታናሽቱ እኅት ላይ ያስተላለፈው ፍርድ፤
22“አሁንም ኦሆሊባ ሆይ! እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምልሽ ይህ ነው፤ እነዚያን ወዳጆችሽን ተጸይፈሻቸዋል፤ ነገር ግን እነርሱ በአንቺ እንዲነሡ አደርጋለሁ፤ እንዲከቡሽም ወደዚህ አመጣቸዋለሁ። 23ባቢሎናውያንንና ከለዳውያንን ሁሉ አመጣለሁ፤ የፈቆድን፥ የሾዐንና የቆዐንን ወንዶች እንዲሁም አሦራውያንን ሁሉ አመጣለሁ፤ ወጣትነት ያላቸው፥ መልከ ቀና የሆኑ መሳፍንትና የጦር መኰንኖች፥ ታላላቅ ባለሥልጣኖችና ከፍተኛ ማዕርግ ያላቸው እነዚህ ሁሉ በፈረስ ተቀምጠው ይመጣሉ። 24እነርሱም በብዙ ሠረገላና ስንቅ በተጫኑ ጋሪዎች የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት መርተው በማምጣት በሁሉም አቅጣጫ አደጋ ይጥሉብሻል፤ በጋሻና በራስ ቊር እየተከላከሉ ይከቡሻል፤ እኔም ለእነርሱ ፍርድ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም በራሳቸው ሕግ መሠረት ይቀጡሻል። 25እኔ በአንቺ ስለ ተቈጣሁ፤ እነርሱም በቊጣቸው በአንቺ ላይ የፈለጉትን እንዲያደርጉ እፈቅድላቸዋለሁ፤ አፍንጫሽንና ጆሮዎችሽን ይቈርጣሉ፤ ከአንችም የቀሩትን በሰይፍ ይገደላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ከአንቺ ነጥቀው ይወስዳሉ፤ ከአንቺም የቀሩትን በእሳት ያቃጥሉአቸዋል። 26ልብሶችሽን ሁሉ ይገፉሻል፤ ጌጣጌጦችሽንም ሁሉ ይወስዳሉ። 27የዝሙት ሥራሽንና ገና በግብጽ ሳለሽ ጀምሮ የምትፈጽሚያቸውን አሳፋሪ ድርጊቶች ሁሉ እንድትተይ አደርጋለሁ፤ ዳግመኛም ወደ ጣዖቶች አትመለከቺም፤ ስለ ግብጽም አታስቢም።”
28ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “በጥላቻ ለምትጸየፊያቸው ሕዝቦች አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ 29-30አንቺን ከመጥላታቸው የተነሣ የደከምሽበትን ሁሉ ይወስዱብሻል፤ እርቃንሽንም አስቀርተው እንደ አመንዝራ ሴት ኀፍረተ ሥጋሽ እንዲጋለጥ ያደርጋሉ፤ የተቃጠለ ፍትወትሽና ዘማዊነትሽ፥ ይህ ሁሉ እንዲደርስብሽ አድርጎአል፤ ለሕዝቦች ሁሉ የፍትወት መጠቀሚያ ዘማዊት ሆነሽ በጣዖቶቻቸው ራስሽን አረከስሽ። 31የእኅትሽን አካሄድ ስለ ተከተልሽ እርስዋ የጠጣችውን የቅጣት ጽዋ እንድትጠጪ አደርግሻለሁ።”
32ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እነሆ ከእኅትሽ ጽዋ ትጠጪአለሽ፤
እርሱም ትልቅና ጥልቀት ያለው ነው፤
ሰው ሁሉ መቀለጃና ማፌዣ ያደርግሻል፤
ጽዋውም ብዙ የሚይዝ ነው።
33አንቺ በስካርና በሐዘን የተሞላሽ ትሆኚአለሽ፤
የእኅትሽ የሰማርያንም የጥፋትና የውድመት ጽዋ ትጠጪአለሽ።
34ምንም ሳታስቀሪ ጨልጠሽ ትጠጪዋለሽ፤
ጽዋውንም ሰባብረሽ በስባሪው በሐዘን ጡቶችሽን ትቈራርጪአለሽ።
እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
35አሁንም ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ስለ ረሳሽኝና ጀርባሽን ስላዞርሽብኝ፥ ስለ ሴሰኛነትሽና ስለ አመንዝራነትሽም መከራ ትቀበዪአለሽ።”
በሁለቱም እኅትማማቾች ላይ የሚመጣ የእግዚአብሔር ፍርድ
36እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! በኦሆላና በኦሆሊባ ላይ ፍርድ ለመስጠት ተዘጋጅተሃልን? ያደረጉትን አጸያፊ ነገር ግለጥላቸው፤ 37ሁለቱም አመንዝሮችና ነፍሰ ገዳዮች ናቸው፤ ያመነዘሩት ከጣዖቶች ጋር ሲሆን፥ የገደሉአቸውም ለእኔ የወለዱአቸውን ልጆች ነው፤ ወንዶች ልጆቼን ለጣዖቶቻቸው ሠውተዋል። 38እነርሱ የፈጸሙት በደል ይህ ብቻ አይደለም፤ ቤተ መቅደሴንም በዚያን ጊዜ አርክሰዋል፤ ሰንበቴንም ሽረዋል። 39ለጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ ልጆቼን በገደሉበት ዕለት ወደ ቤተ መቅደሴ መጥተው አረከሱት፤ እነሆ በቤቴ ያደረጉት ይህ ነው።
40“ወንዶችን ከሩቅ አገር ጋብዘው እንዲያመጡላቸው ደጋግመው መልእክተኞችን ላኩ፤ የፈለጓቸውም ወንዶች መጡላቸው፤ ሁለቱ እኅትማማቾች ገላቸውን ታጠቡ፤ ዐይናቸውን ተኳሉ፤ ጌጣጌጦቻቸውንም አደረጉ፤ 41በተዋቡም ድንክ አልጋዎች ላይ በፊት ለፊታቸው ተቀመጡ፤ እኔ የሰጠኋቸው ዕጣንና የወይራ ዘይት ሳይቀር ብዙ መልካም ነገሮችን በጠረጴዛ ላይ ደረደሩ። 42የብዙ ሁከተኞች ድምፅ በአካባቢአቸው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር ከበረሓ የመጡ ሰካራሞች ነበሩ፤ ሰካራሞቹም በሴቶቹ ክንዶች ላይ አምባር፥ በራሶቻቸውም ላይ የተዋቡ አክሊሎችን አደረጉላቸው። 43እኔም በልቤ ‘እነዚህ ወንዶች ዝሙት የሚፈጽሙት በአመንዝራነት ሰውነትዋ ካለቀ ሴት ጋር ነው’ አልኩ። 44ወንዶች ወደ አመንዝራ ሴቶች እንደሚሄዱ ሁሉ፥ እነዚያም ከበረሓ የመጡ ወንዶች ኦሆላና ኦሆሊባ ከተባሉት ከእነዚያ ከረከሱ ሴቶች ጋር አመነዘሩ። 45ማመንዘር ስለ ለመዱና እጆቻቸውም በደም ስለ ተበከሉ፥ በእነዚያ በአመንዝሮቹና በነፍሰ ገዳዮቹ ላይ ጻድቃን ይፈርዱባቸዋል።”
46ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “በእነርሱ ላይ ሁከተኞችን ሰብስብ፤ እነርሱንም ለብዝበዛና ለሽብር አሳልፈህ ስጣቸው። 47ሁከተኞችንም በድንጋይ ይውገራቸው፤ በሰይፍም ይቈራርጧቸው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ይግደሉ። ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥሉ። 48እናንተ ሁለት እኅትማማቾች እንዳመነዘራችሁ ሁሉ ሴቶች ከእንግዲህ ወዲህ እንዳያመነዝሩ መቀጣጫ ይሆን ዘንድ ከምድሪቱ ሁሉ ላይ የሴሰኝነት ስድነት እንዲወገድ አደርጋለሁ። 49እናንተም ሁለት እኅትማማቾች ስለ ስድነታችሁና ለጣዖቶች በመስገድ ስለ ፈጸማችሁት ኃጢአት እቀጣችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ ልዑል እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 23: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997