የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 37

37
የደረቁ አጥንቶች የተከማቹበት ሸለቆ
1የእግዚአብሔር ኀይል በእኔ ላይ መጣ፤ የእርሱም መንፈስ እኔን ወስዶ ብዙ አጥንቶች በተከማቸበት ሸለቆ ውስጥ አኖረኝ፤ 2በአጥንቶቹ መካከል አዙሮ አሳየኝ፤ በዚያም እጅግ የደረቁ በጣም ብዙ አጥንቶች ነበሩ። 3እርሱም “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ አጥንቶች ዳግመኛ ሕይወት የሚያገኙ ይመስልሃልን?” አለኝ።
እኔም “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ይህን የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ” አልኩት።
4እርሱም እንዲህ አለ፦ “ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ብለህ ትንቢት ተናገር፦ እናንተ ደረቅ አጥንቶች የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 5እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በውስጣችሁ እስትንፋስ በማስገባት እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ። 6ጅማትና ሥጋ በመስጠት ቆዳ አለብሳችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አስገብቼ እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”
7እኔም በታዘዝኩት መሠረት ትንቢት ተናገርኩ፤ መናገርም እንደ ጀመርኩ የመንኰሻኰሽ ድምፅ ሰማሁ፤ አጥንቶቹም እርስ በርሳቸው እየተገጣጠሙ መያያዝ ጀመሩ። 8በመመልከት ላይ ሳለሁም አጥንቶቹ በጅማትና በሥጋ እንዲሁም በቈዳ ተሸፈኑ፤ እስትንፋስ ግን አልነበራቸውም።
9እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለነፋስ ትንቢት ተናገር፤ ነፋስ ከአራቱም ማእዘን መጥቶ ሕይወት እንዲያገኙ በእነዚህ በድኖች ላይ እንዲነፍስ ንገረው።”
10እኔም በታዘዝኩት መሠረት ትንቢት ተናገርሁ፤ በእነርሱ ሁሉ ውስጥ እስትንፋስ ገባባቸው፤ ሁሉም ሕይወት አግኝተው ቆሙ፤ እጅግ ብዙ ሠራዊትም ሆኑ። #ራዕ. 11፥11።
11እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የእስራኤል ሕዝብ እኮ ልክ እንደእነዚህ አጥንቶች ናቸው፤ እነርሱ ‘እነሆ፥ አጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋ ቈርጠናል፤ የእኛ ጉዳይ አልቆለታል’ ይላሉ። 12ስለዚህም ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር መቃብራቸውን ከፍቼ እነርሱን በማውጣት ወደ እስራኤል ምድር የምመልሳቸው መሆኔን ንገራቸው። 13ሕዝቤ የተቀበሩበትን መቃብር ሁሉ ከፍቼ በማወጣቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ። 14እስትንፋሴን በእነርሱ ውስጥ አገባለሁ፤ በሕይወትም እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ፤ በገዛ ምድራቸውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይህን የተናገርኩና የማደርገውም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
የይሁዳና የእስራኤል በአንድ መንግሥት መጠቃለል
15እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 16“የሰው ልጅ ሆይ! አንድ በትር ወስደህ ‘በእርሱ ላይ ለይሁዳና ከእርሱ ጋር ለተባበሩ እስራኤላውያን’ ብለህ ጻፍ፤ ከዚያም ሌላ በትር ወስደህ በእርሱ ላይ ‘ለዮሴፍ ማለት ለኤፍሬምና ከእርሱ ጋር ለተባበሩ እስራኤላውያን’ ብለህ ጻፍ። 17ከዚህ በኋላ በእጅህ አንድ ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን በትሮች በአንድነት አገጣጥመህ ያዛቸው። 18ሕዝብህም ይህ ምን መሆኑን እንድትነግራቸው በሚጠይቁህ ጊዜ፥ 19ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል ብለህ ንገራቸው፦ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን ከእነርሱ ጋር የተባበሩትን የእስራኤልን በትር ወስጄ አንድ በትር እንዲሆኑ ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥማቸውና በእጄ አንድ ይሆናሉ።
20“የጻፍክባቸውንም ሁለቱን በትሮች በእጅህ ይዘህ ሕዝቡ እንዲያዩአቸው አድርግ። 21እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕዝቤን ሁሉ ከተበተኑባቸው ሕዝቦች መካከል በአንድነት ሰብስቤ ወደገዛ ምድራቸው መልሼ የማመጣቸው መሆኔን ንገራቸው። 22በእስራኤል ምድርና በተራሮችዋ አንድ መንግሥት እንዲሆኑ አደርጋለሁ፤ ሁሉንም በአንድነት የሚያስተዳድር አንድ ንጉሥ ይኖራቸዋል፤ ዳግመኛ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፤ መንግሥታቸውም በሁለት አይከፈልም። 23ዳግመኛ በጣዖቶቻቸው፥ በአጸያፊ ነገሮቻቸው፥ ወይም በሌሎች ኃጢአቶቻቸው ራሳቸውን አያረክሱም፤ ከወደቁበት ክሕደት አውጥቼ አነጻቸዋለሁ። በዚያን ጊዜ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ። 24እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት ያለ ንጉሥ ይኖራቸዋል፤ በአንድ መሪ ሥር ተጠቃለው ሕጎቼንና ሥርዓቴን በታማኝነት ይፈጽማሉ። #ሕዝ. 34፥24። 25ለአገልጋዬ ለያዕቆብ በሰጠሁትና የቀድሞ አባቶቻቸውም በኖሩባት ምድር ይኖራሉ፤ በዚያችም ምድር እነርሱና ልጆቻቸው ዘሮቻቸውም ሳይቀሩ ለዘለዓለም ይኖራሉ፤ እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት ያለ ንጉሥ በእነርሱ ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል። 26ከእነርሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ያም ቃል ኪዳን ዘለዓለማዊ ነው፤ እነርሱንም እንደገና መሥርቼ የሕዝቡን ቊጥር አበዛለሁ፤ ቤተ መቅደሴንም ለዘለዓለም ጸንቶ በሚቈይበት ስፍራ በምድራቸው አኖራለሁ። 27እኔም በዚያ ከእነርሱ ጋር እኖራለሁ፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። #2ቆሮ. 6፥16፤ ራዕ. 21፥3። 28ቤተ መቅደሴ በመካከላቸው ለዘለዓለም እንዲኖር በማደርግበት ጊዜ፤ ለእኔ እስራኤልን ለራሴ የተለየ ሕዝብ የማደርግ መሆኔን አሕዛብ ያውቃሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ