የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 39

39
የጎግ መሸነፍ
1ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የሜሼክና የቱባል ሕዝብ ገዢ በሆነው በጎግ ላይ ትንቢት ተናገርበት፤ በእርሱም ላይ የተነሣሁ መሆኔን ንገረው። 2አቅጣጫውን አስለውጬ ሩቅ ከሆነው ከሰሜን አገር ገፋፍቼ በእስራኤል ተራራዎችም ላይ እንዲዘምት አደርገዋለሁ፤ 3ከዚያም በኋላ እርሱን መትቼ ቀስቱን ከግራ እጁ፥ ፍላጻውንም ከቀኝ እጁ አስጥለዋለሁ። 4ጎግና ሠራዊቱ፥ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰለፉ የጦር ጓደኞቹ ሁሉ ሞተው በእስራኤል ተራራዎች ላይ ይወድቃሉ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ እንዲሆን አደርገዋለሁ። 5በአውላላ ሜዳ ላይ ወድቀው ይቀራሉ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 6በማጎግ ምድርና በባሕር ዳርቻዎች ሰዎች ያለ ስጋት በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ እሳት አቀጣጥላለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሁሉም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ። 7ቅዱስ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል ዘንድ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስሜ እንዲሰደብ አልፈቅድም፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቦች ሁሉ እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ መሆኔን ያውቃሉ።”
8ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እየመጣ ነው፤ በእርግጥ ይፈጸማል፤ ይመጣል ብዬ የተናገርኩት ቀን ይህ ነው። 9በእስራኤል ከተሞች የሚኖሩ ሕዝብ ወጥተው የተጣለውን የጦር መሣሪያ ሁሉ ለእሳት ማገዶ እንዲሆን ይሰበስባሉ፤ ጋሻውን፥ ቀስቱን፥ ፍላጻውን፥ ጦሩንና ዱላውን ሁሉ ሰብስበው ያነዱታል፤ ለሰባት ዓመት የሚበቃም ማገዶ ይኖራቸዋል። 10ስለዚህም ከየስፍራው የማገዶ እንጨት መሰብሰብም ሆነ፥ ከየጫካውም ዛፍ መቊረጥ አያስፈልጋቸውም፤ ምክንያቱም ወድቆ የቀረውን የጦር መሣሪያ ሁሉ ሰብስበው ማንደድ ይችላሉ፤ ቀድሞ የበዘበዙአቸውንና የዘረፉአቸውን አሁን በተራቸው መበዝበዝና መዝረፍ ይችላሉ፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።
የጎግ መቃብር
11ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ይህ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ በእስራኤል ምድር በሚገኘው፥ ከሙት ባሕር በስተ ምሥራቅ ባለው በመንገደኞች ሸለቆ ውስጥ፥ ለጎግ የመቃብር ቦታ እሰጠዋለሁ፤ እርሱም ከብዛቱ የተነሣ መተላለፊያ መንገዱን ይዘጋል፤ ጎግና ሠራዊቱ ሁሉ በዚያ ይቀበራሉ፤ ስለዚህም ያ ሸለቆ ‘የጎግ ሠራዊት ሸለቆ’ ተብሎ ይጠራል። 12ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ያንን ሁሉ ሬሳ ቀብረው ምድሪቱን እንደገና ለማጽዳት ሰባት ወራት ይፈጅባቸዋል። 13በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ሬሳውን በመቅበር ይተባበሩአቸዋል፤ የእኔ ክብር በሚገለጥበት ቀን ለእነርሱም ክብር ይሆንላቸዋል፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 14ከሰባት ወራትም በኋላ በምድር ላይ የተረፉ ሬሳዎች ቢኖሩ በየስፍራው በመዘዋወር እየፈለጉ በመቅበር ምድሪቱን የሚያጸዱ ሰዎች ይመደባሉ። 15በሀገሪቱም ውስጥ ሲዘዋወሩ የሰው ዐፅም በሚያገኙበት ጊዜ በጐኑ ምልክት አድርገውበት ያልፋሉ፤ መቃብር ቆፋሪዎችም መጥተው በሐሞን ጎግ ሸለቆ ይቀብሩታል። 16በዚህም ዐይነት ምድሪቱ እንደገና ትጸዳለች፤ በዚያም አቅራቢያ ሐሞና ተብላ የምትጠራ ከተማ ትኖራለች።”
17ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ለተለያዩ የአሞራ ዘሮችና ለአራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ ‘በእስራኤል ተራራዎች ላይ በማዘጋጅላችሁ ታላቅ የመሥዋዕት በዓል ሥጋን ለመብላትና ደምን ለመጠጣት ከየአቅጣጫው ተሰብስባችሁ ኑ።’ #ራዕ. 19፥17-18። 18እንደ ቅልብ የባሳን ጠቦትና ሙክት ፍየልና ኰርማ የሆኑትን የኀያላን ሰዎችን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድር ልዑላንንም ደም ትጠጣላችሁ። 19እኔ በማዘጋጅላችሁ የመሥዋዕት በዓል ላይ እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ። 20እኔ ከማቀርብላቸው ማእድ የፈረሶችንም ሆነ የፈረሰኞችን፥ የወታደሮችንም ሆነ የሌሎችን ጦረኞች ሥጋ እስከሚጠግቡ ይመገባሉ፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።
የእስራኤል መመለስ
21ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ክብሬን በሕዝቦች መካከል እገልጣለሁ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ተግባራዊ ያደረግኹትን ፍርዴንና እነርሱን የቀጣሁበትን ኀይሌን ያያሉ። 22እስራኤላውያንም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንኩ ያውቃሉ። 23እስራኤላውያን ተማርከው የሄዱትም እኔን በመበደላቸው ምክንያት መሆኑን ሕዝቦች ሁሉ ያውቃሉ፤ እኔ ችላ ስላልኳቸው ጠላቶቻቸው በጦርነት ድል አድርገው ሁላቸውንም ገድለዋቸዋል። 24እንደ ርኲሰታቸውና እንደ በደላቸው አደረግሁባቸው፤ ርዳታም አላደረግሁላቸውም።”
25ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አሁን ግን የያዕቆብ ልጆች ለሆኑት ለእስራኤል ሕዝብ ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ እንደገናም አበለጽጋቸዋለሁ፤ ቅዱስ ስሜም እንዳይሰደብ እከላከላለሁ። 26የሚያስፈራቸው ነገር ሳይኖር በገዛ ምድራቸው በሰላም ይኖሩ በነበረ ጊዜ የፈጸሙትን አሳፋሪ ተግባርና ለእኔ አለመታመናቸውን ሁሉ ይረሳሉ። 27እነርሱን ከሕዝቦች መካከል ስመልሳቸውና ከጠላቶቻቸው አገሮችም ብዙ ሕዝቦች እያዩ ስሰበስባቸው በእነርሱ አማካይነት ቅድስናዬን እገልጣለሁ። 28ተማርከው ወደ ስደት እንዲሄዱ ያደረግኋቸው እኔ ብሆንም እንኳ አሁን ከእነርሱ አንድም ሰው ወደኋላ ሳይቀር ወደ ገዛ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጌአለሁ። ስለዚህ ሕዝቤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው መሆኔን ያውቃሉ። 29መንፈሴን በእስራኤል ሕዝብ ላይ አፈሳለሁ፤ ዳግመኛም ችላ አልላቸውም፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ