የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 41

41
1ቀጥሎም የቤተ መቅደሱ ማእከል ወደ ሆነው የተቀደሰ ስፍራ አስገባኝ፤ ወደ እርሱ የሚወስደውንም መተላለፊያ ሲለካ የሁለቱ ጐን ትይዩ ርዝመት ስድስት ክንድ ሆነ። 2ወርዱም ዐሥር ክንድ ሆነ፤ በግራና ቀኝ የሚገኙትም ግንቦች የእያንዳንዱ ውፍረት አምስት ክንድ ነበር፤ የተቀደሰው ስፍራ ሲለካ ርዝመቱ አርባ ክንድ፥ ወርዱም ኻያ ክንድ ሆነ።
3ከዚያም አልፎ ወደ ውስጠኛው ክፍል ገባ፤ ወደ እርሱ የሚያስገባውንም መተላለፊያ ሲለካው ርዝመቱ ሁለት ክንድ ወርዱ ስድስት ክንድ ሆነ፤ በግራና ቀኝ የሚገኙትም ግንቦች የእያንዳንዱ ውፍረት ሰባት ክንድ ሆነ። 4ከመካከለኛው ክፍል ባሻገር ያለውን ውስጠኛ ክፍል ከማእዘን እስከ ማእዘን ሲለካ ርዝመቱ ኻያ ክንድ ወርዱም ኻያ ክንድ ሆነ፤ ከዚያም በኋላ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ።
በቤተ መቅደሱ ጥግ ዙሪያውን የተሠሩ ክፍሎች
5ያ ሰው የቤተ መቅደሱን ሕንጻ የውስጠኛ ግንብ ሲለካ ውፍረቱ ስድስት ክንድ ሆነ፤ ከዚህም ግንብ ጋር ተጠግተው በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የተሠሩና የእያንዳንዱ ወርድ አራት ክንድ የሆነ ብዙ ክፍሎች ነበሩ። 6እነዚህም ክፍሎች አንዱን በአንዱ ላይ በመቀጠል ሦስት ፎቅ ሆነው ተሠርተው፥ እያንዳንዱ ፎቅ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩት፤ በእያንዳንዱ ፎቅ ላይ ያለው የቤተ መቅደሱ ውጫዊ ግንብ በታችኛው ካለው ፎቅና ግንብ ይልቅ የሳሳ ነበር፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በቤተ መቅደሱ ሕንጻ ላይ ሳያርፍ፥ ክፍሎቹ የተደገፉት በዚያው በዋናው ግንብ ስለ ነበር ነው። 7የታችኛው ግድግዳ ከፎቁ ግድግዳ የወፈረ ነው፤ ሆኖም ከውጪ ሲመለከቱት ከላይ እስከ ታች ያለው ግድግዳ እኩል ውፍረት ያለው ይመስላል። ግድግዳዎቹ ከታች ወደላይ እየሳሱ ስለሚሄዱ ወደ ላይ በተወጣ ቊጥር ክፍሎቹ እየሰፉ ይሄዳሉ። መወጣጫዎቹም ከምድር ወደ ላይኛው ፎቅ የሚወጡት በመካከለኛው ፎቅ በኩል አድርገው ነው። 8የቤተ መቅደሱ መሠረት ስድስት ክንድ ከፍ ያለ ነበር፤ የውጪዎቹ ክፍሎችም መሠረት በዚያው ልክ ነበር። 9-10የውጪው ክፍሎች ግድግዳ ውፍረት አምስት ክንድ ነበር፤ ከቤተ መቅደሱ ጐን ካሉት ክፍሎችና ከሚቀጥሉት ሕንጻዎች መካከል ባዶ ቦታ ነበር፤ የዚህም ባዶ ቦታ ስፋት በሃያ ክንድ ቤተ መቅደሱን ይዞር ነበር። 11በቤተ መቅደሱ ጐን ያሉት ክፍሎች በሮቻቸው የሚከፈቱት ወደ ባዶው ቦታ አቅጣጫ ሲሆን አንዱ በሰሜን በኩል ሌላው ደግሞ በደቡብ በኩል ይከፈታል፤ የተተወውም ባዶ ቦታ ዙሪያው አምስት ክንድ ነበር።
12በምዕራብ በኩል በባዶው ቦታ ጫፍ አንድ ሕንጻ አለ፤ የሕንጻው ግድግዳ ውፍረት ዙሪያው አምስት ክንድ፥ ወርዱ ሰባ ክንድ፥ ርዝመቱ ደግሞ ዘጠና ክንድ ነው።
የቤተ መቅደሱ ሕንጻ አሠራርና ልክ
13ያ ሰው ቤተ መቅደሱን ሲለካ አንድ መቶ ክንድ ሆኖ አገኘው፤ ከቤተ መቅደሱ በኋላ በኩል ባዶው ቦታውን አቋርጦ በስተ ምዕራብ እስካለው የሕንፃው መጨረሻ ድረስ ሲለካ በአንድነት ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። 14ከቤተ መቅደሱም በምሥራቅ በኩል ባለው በር ፊት ለፊት ያለው ርዝመት በሁለቱም አቅጣጫ ያሉትን ክፍት ቦታዎች ጨምሮ መቶ ክንድ ሆነ፤ 15በሁለቱም በኩል ያሉትን መተላለፊያዎች ጨምሮ በምዕራብ በኩል ያለውን የሕንጻውን ርዝመት ሲለካው አንድ መቶ ክንድ ሆነ።
የቤተ መቅደሱ መተላለፊያ፥ ቅዱሱ ስፍራና ወደ ውስጥ ዘልቆ የሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን፥ 16ሦስቱም ወደ ውስጥ ገባ ያሉ በዙሪያቸው ክፈፍ ያሉአቸው መስኮቶች ነበሩአቸው፤ ግድግዳዎቻቸውም ከወለሉ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት የተለበዱ ነበሩ፤ የመስኮቶቹ መዝጊያዎችም በዚሁ የተሠሩ ነበሩ። 17እንዲሁም በውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ የውስጥ ክፍል የሚያስገባው ከበር በላይ ያለው ስፍራም ተለብዶ ነበር፤ በውስጠኛውና በመካከለኛው ክፍል ያሉት ዙሪያ ግድግዳዎች ቅርጽ ባለው መለበጃ የተለበዱ ነበሩ። 18በመለበጃውም ላይ ያለው ቅርጽ የዘንባባ ዛፎችና የኪሩቤል ስዕል ነበር፤ በክፍሉም ዙሪያ የዘንባባና የኪሩቤል ሥዕሎች ተሰባጥረው ተስለውበታል፤ እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊቶች ነበሩት፤ 19በአንድ በኩል የሰው ፊት ቅርጽ ያለው ወደ ዘንባባው ሲመለከት፥ በሌላም አቅጣጫ የደቦል አንበሳ ቅርጽ ያለው ወደ ዘንባባው ዛፍ ይመለከት ነበር። እነርሱም በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ተቀርጸው ነበር። 20ከወለሉ አንሥቶ ከበሮቹ በላይ እስካለው ስፍራ ድረስ በግድግዳዎቹ ላይ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ተቀርጸው ነበር። 21የመቅደሱም የበር መቃኖች ቅርጽ ሁሉ እኩልነት ያለው አራት ማእዘን ነበር።
ከእንጨት የተሠራው መሠዊያ
22በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ ፊት ለፊት፥ ከእንጨት የተሠራ መሠዊያ የሚመስል ነገር ይታይ ነበር፤ እርሱም እኩልነት ያለው አራት ማእዘን ሲሆን፥ እያንዳንዱ ማእዘን ሁለት ክንድ ነበር፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ነበር፤ የማእዘን መደገፊያ ምሰሶዎቹ፥ መሠረቱና ጐኖቹ ሁሉ ከእንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ ያም ሰው “ይህ በእግዚአብሔር ፊት የሚገኝ ጠረጴዛ ነው” አለኝ።
በሮቹ
23የተቀደሰው ቦታና ቅድስተ ቅዱሳኑ ድርብ መዝጊያዎች አሉአቸው። 24እያንዳንዱ መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት፤ ይህም ማለት ለያንዳንዱ መዝጊያ በመግፋት ወይም በመሳብ በሁለት በኩል የሚከፈቱ ሁለት ሳንቃዎች ማለት ነው። 25በግድግዳዎቹ ላይ እንደተቀረጸው በተቀደሰው ስፍራ በር ላይም ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ተቀርጸው ነበር። በመግቢያው ክፍል ፊት ለፊት በስተውጪ ከእንጨት የተሠራ አጎበር ነበር። 26በመግቢያው ክፍል ግድግዳዎች፥ በሁለቱም በኩል ወደ ውስጥ ገባ ያሉ መስኮቶች የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ነበሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ