ትንቢተ ሕዝቅኤል 44
44
የምሥራቁ ቅጽር በር አገልግሎት
1ያም ሰው በስተ ምሥራቅ በኩል ወደሚገኘው ወደ ቤተ መቅደሱ ውጪ በር ወሰደኝ፤ በሩም ተዘግቶ ነበር፤ 2እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ በር እንደ ተዘጋ ይኖራል እንጂ ከቶ አይከፈትም፤ የእስራኤል አምላክ እኔ እግዚአብሔር የገባሁበት ስለ ሆነ፥ ማንም በዚህ በር መጠቀም አይችልም፤ ስለዚህም እንደ ተዘጋ ይኖራል። 3የሆነ ሆኖ የሕዝቡ መሪ የተቀደሰውን የመሥዋዕት ኅብስት ለመብላት በዚያ መቀመጥ ይችላል፤ በመግቢያውም ክፍል ውስጠኛ ጫፍ በሚገኘው መተላለፊያ በኩል መግባትና መውጣት ይፈቀድለታል።”
ወደ ቤተ መቅደሱ ስለ መግባትና ከዚያም ስለ መውጣት የተደነገገ ሕግና ሥርዓት
4ከዚያም በኋላ ያ ሰው በሰሜኑ ቅጽር በር በኩል አድርጎ ወደ ቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ወሰደኝ፤ በዚያም ሆኜ ስመለከት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በክብሩ ተሞልቶ አየሁ፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ፤ 5እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የምትሰማውንና የምታየውን ነገር ሁሉ ልብ ብለህ አስተውለው፤ እነሆ እኔ ስለ ቤተ መቅደሱ ሕግና ሥርዓት ሁሉ እነግርሃለሁ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ መግባትና መውጣት የሚፈቀድላቸው ምን ዐይነት ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውል።
6“ ለዐመፀኞቹ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ ‘የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፥ ክፉ አድራጎታችሁን ሁሉ አስወግዱ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 7ስብንና ደምን ለእኔ የምግብ ቊርባን አድርጋችሁ በምታቀርቡበት ጊዜ ሊታዘዙኝ ፈቃደኞች ያልሆኑትን ያልተገረዙ ባዕዳን ወደ ተቀደሰው ስፍራዬ በማስገባት ቤተ መቅደሴን አርክሳችኋል፥ በረከሰውም ተግባራችሁ ሁሉ ቃል ኪዳኔን አፍርሳችኋል። 8የተቀደሰ ቊርባኔንም በኀላፊነት አልጠበቃችሁም፤ እንዲያውም በተሰጣችሁ የኀላፊነት ቦታ ላይ ባዕዳንን መደባችሁበት።’ ”
9ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሊታዘዙኝ ፈቃደኞች ያልሆኑት ያልተገረዙ ባዕዳን ሁሉ፥ በእስራኤል ሕዝብ መካከል የሚኖሩት እንኳ ቢሆኑ ወደተቀደሰው ስፍራዬ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም።”
የሌዋውያን ከክህነት አገልግሎት መባረር
10እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ከሌሎቹ የእስራኤል ሕዝብ ጋር እኔን ከድተው ለጣዖታት የሰገዱትን ሌዋውያንን እቀጣለሁ፤ 11እነርሱ በቤተ መቅደሱ በር ጠባቂነት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሰዎች የሚያቀርቡአቸውን መሥዋዕቶች በማረድ፥ እንዲሁም ሰዎችን በማገልገል እንዲሠሩ ይፈቅድላቸዋል። 12ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው የጣዖት አምልኮ ሥርዓት መሪዎች በመሆን ሕዝቡን ወደ ኃጢአት ስለ መሩ መቀጣት እንደሚገባቸው በራሴ ምዬአለሁ” ይላል ልዑል እግዚአብሔር። 13“በክህነት ለማገልገል ወደ እኔ አይቀርቡም፤ በጣም ወደ ተቀደሰው ቅዱስ ቊርባኔም አይቀርቡም፤ እነርሱም ለፈጸሙት አጸያፊ ተግባራቸው አሳፋሪ ውጤት ተጠያቂዎች ይሆናሉ። 14ስለዚህ በክህነት ሳይሆን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን ሌላውን ተግባር ሁሉ እንዲያከናውኑ እመድባቸዋለሁ።”
ለክህነት አገልግሎት ተገቢ የሆኑ ካህናት
15ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ሌሎቹ የእስራኤል ሕዝብ እኔን ከድተው ከፊቴ ሲርቁ፥ በቤተ መቅደስ በታማኝነት ጸንተው እኔን ሲያገለግሉ የኖሩና ነገዳቸው ከሌዊ ወገን ሆኖ ከሳዶቅ የተወለዱ ካህናት አሉ፤ ስለዚህም ስብና የመሥዋዕት ደም በማቅረብ በፊቴ ቆመው ሊያገለግሉኝ የሚገባቸው እነርሱ ናቸው፤ 16እኔን ለማገልገል ወደ ተቀደሰው ቦታዬ የሚገቡና ወደ ገበታዬ የሚቀርቡ እነርሱ ናቸው። እነርሱም ትእዛዜን ይጠብቃሉ። 17በቤተ መቅደሱ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያደርሰውን ቅጽር በር በሚገቡበት ጊዜ ከበፍታ የተሠራ ልብስ መልበስ ይኖርባቸዋል፤ በውስጠኛው አደባባይም ሆነ በቤተ መቅደስ በሚያገለግሉበት ጊዜ ማናቸውንም ከበግ ጠጒር የተሠራ ነገር መልበስ የለባቸውም። #ዘፀ. 28፥39-43፤ ዘሌ. 16፥4። 18በራሳቸው ላይ ከበፍታ የተሠራ መጠምጠሚያ ይጠምጥሙ፤ በወገባቸውም ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ልብስ ይልበሱ፤ ማናቸውም ላብ የሚያመጣ መታጠቂያ አይታጠቁ። 19ሕዝቡ ወደሚገኙበት ወደ ውጪው አደባባይ ከመውጣታቸው በፊት በቤተ መቅደስ ለአገልግሎት የተጠቀሙባቸውን አልባሳት አውልቀው በተቀደሱት ዕቃ ቤቶች ማኖርና ለራሳቸውም ሌላ ልብስ መልበስ አለባቸው፤ ይህንንም የሚያደርጉት ሕዝቡ ያልተፈቀደለትን የእነርሱን የተቀደሰ ልብስ ነክቶ እንዳይጐዳ ነው። #ዘሌ. 16፥23።
20“ካህናቱ ራሳቸውን መላጨትም ሆነ ጠጒራቸውን ማሳደግ አይገባቸውም፤ ነገር ግን ፀጒራቸውን በሚገባ ሁኔታ ያስተካክሉ። #ዘሌ. 21፥5። 21ካህናቱ ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገቡበት ጊዜ ማናቸውንም ዐይነት የወይን ጠጅ አይጠጡ። #ዘሌ. 10፥9። 22ካህን የሆነ ሁሉ ባልዋ የሞተባትን ወይም ከባልዋ የተፋታችውን ሴት ማግባት አይፈቀድለትም፤ ነገር ግን ድንግል የሆነችውን እስራኤላዊት ልጃገረድ ወይም ካህን የሆነ ባልዋ የሞተባትን ሴት ማግባት ይችላል። #ዘሌ. 21፥7፤13-14።
23“ካህናቱ ለሕዝቤ ቅዱስ የሆነውንና ያልሆነውን ንጹሕ የሆነውንና ርኩስ የሚባለውን ነገር እንዲለዩ ያስተምሩአቸው። #ዘሌ. 10፥10። 24ሕግን በሚመለከት አከራካሪ ነገር በሚነሣበት ጊዜ፥ ደንቡ በሚያዝዘው መሠረት ካህናቱ ይወስኑላቸው፤ በሕጌና ሥርዓቴ መሠረት በዓሎቼን፥ እንዲሁም ዕለተ ሰንበትን በመቀደስ ይጠብቁ።
25“ከወላጆቹ አንዱ፥ ከልጆቹ አንዱ፥ ወይም ወንድሙ ወይም ያላገባች እኅቱ ካልሆኑ በቀር ማንኛውም ካህን የሌላ ሰው ሬሳ በመንካት ራሱን ማርከስ አይገባውም፤ #ዘሌ. 21፥1-4። 26ይህን ካደረገ ግን ከነጻም በኋላ እንኳ ሰባት ቀን መቈየት አለበት፤ 27ለአገልግሎት ወደ ውስጠኛው አደባባይ፥ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን ለኃጢአቱ መሥዋዕት ያቅርብ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
28“ይህ የካህናቱ ርስት ነው፤ ይህም ማለት እኔ ርስታቸው ነኝ፤ እኔ ይዞታቸው ስለ ሆንኩ በእስራኤል ምንም ይዞታ አይሰጣቸውም። #ዘኍ. 18፥20። 29የእህሉ መሥዋዕት፥ የኃጢአትና የበደል ስርየት መሥዋዕት ለእነርሱ ምግብ ይሁንላቸው፤ በእስራኤል ምድር ለእኔ ተለይቶ የተቀደሰውን ማናቸውንም መባ ሁሉ ይቀበሉ። #ዘኍ. 18፥8-19። 30የመከር መጀመሪያ የሆነውን ያማረውን በኲራትና ለእኔ የቀረበውን ስጦታ ሁሉ ካህናቱ ይውሰዱ፤ ሕዝቡም ሁልጊዜ እህል ሲፈጩ የዱቄቱን በኲራት ለካህናቱ መባ አድርገው ያበርክቱ፤ እኔም ይህንን ሁሉ የሚያደርጉትን ሕዝብ ቤታቸውን በበረከት እሞላዋለሁ። 31ካህናቱ ሞቶ የተገኘውን ወይም ሌላ አውሬ የገደለውን የወፍ ወይም የእንስሳ ሥጋ አይብሉ።” #ዘሌ. 25፥10።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 44: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997