ትንቢተ ሕዝቅኤል 6
6
እግዚአብሔር የጣዖት አምልኮን መቃወሙ
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ወደ እስራኤል ተራራዎች ተመልከት፤ በእነርሱም ላይ ትንቢት ተናገር። 3የእስራኤል ተራራዎች የልዑል እግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ ንገራቸው፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምናገረውን ተራራዎች፥ ኮረብቶችንና ገደላማ ሸለቆዎች ሁሉ ይስሙ፤ ሕዝቦች ለጣዖቶች የሚሰግዱባቸውን ከፍተኛ ቦታዎች ሁሉ የሚያጠፋ ሰይፍ እልካለሁ። 4መሠዊያዎች ሁሉ ይፈርሳሉ፤ የዕጣን ማቅረቢያዎች ሁሉ ይሰባበራሉ፤ የተገደሉትም ሰዎች በጣዖቶቻቸው ፊት ይጣላሉ። 5የእስራኤል ሕዝብ ሬሳቸው በጣዖቶቻቸው ፊት እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤ አጥንቶቻቸውንም በየመሠዊያቸው ዙሪያ እበትነዋለሁ። 6የምትኖሩባቸው ከተሞቻችሁ ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ የመስገጃ ከፍተኛ ቦታዎቻችሁም ይፈርሳሉ፤ መሠዊያዎቻችሁ ፈርሰው ውድማ ይሆናሉ፤ ጣዖቶቻችሁ ተንኰታኲተው ይወድቃሉ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሰባበራሉ፤ የሠራችሁት ነገር ሁሉ እንዳልነበረ ይሆናል። 7የተገደሉት በአካባቢያችሁ ይጣላሉ፤ ከዚያ በኋላ እናንተ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።
8“ነገር ግን ጥቂቶቻችሁ እንድትተርፉ አደርጋለሁ፤ ጥቃቶቻችሁ ወደ ሌሎች ሕዝቦች በመሄድ ከጦርነት አምልጣችሁ በተለያዩ አገሮች ትበተናላችሁ። 9ከሞት ያመለጣችሁት እናንተ ተማርካችሁ በሄዳችሁበት ሕዝቦች መካከል ታስታውሱኛላችሁ፤ የምታስታውሱኝም ከእኔ በራቀው ሥርዓተ አልባ በሆነው ክፉ ልባችሁና ሥርዓተ አልባ በሆነው ዐይናችሁ ጣዖቶችን በመመልከት ስላሳዘናችሁኝ ነው። በርኩስ ድርጊቶቻችሁም ላደረጋችሁት ክፉ ነገር ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። 10እኔ እግዚአብሔር መሆኔንና ጥፋት እንደማመጣባቸው የሰጠሁት ማስጠንቀቂያ ሁሉ ከንቱ ዛቻ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ።”
11ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር ስለሚመቱ ስለ እስራኤላውያን ክፉ ርኲሰት ሁሉ ወዮ! እያላችሁ እጆቻችሁን እያማታችሁና በእግሮቻችሁ እየረገጣችሁ ሐዘናችሁን ግለጡ! 12በሩቅ ያሉት ታመው ይሞታሉ፤ በቅርብ ያሉትም በጦርነት ይገደላሉ፤ ከዚያ የሚተርፉትም በራብ ያልቃሉ፤ በዚህም ዐይነት ኀይል የተሞላበትን ቊጣዬን በእነርሱ ላይ እፈጽማለሁ። 13ሬሳዎች በጣዖቶችና በመሠዊያዎች ዙሪያ ይከመራሉ፤ በከፍተኛ ኰረብቶችና በተራሮች ጫፍ ላይ፥ እንዲሁም በየለምለሙ ዛፍና በየትልልቁ ወርካ ሥር ለጣዖቶቻቸው መልካም ሽታ ባቀረቡባቸው ስፍራዎች ሁሉ ሬሳዎች ይወድቃሉ፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ። 14በእርግጥም እጄን ዘርግቼ አገራቸውን አጠፋታለሁ፤ ከደቡባዊው በረሓ አንሥቶ በሰሜን በኩል እስከምትገኘው እስከ ሪብላ ከተማ ድረስ ባድማ አደርጋታለሁ፤ እስራኤላውያን የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ አንድም ሳይቀር አጠፋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንድ አሆንኩ ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 6: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997