ኦሪት ዘፍጥረት 29
29
ያዕቆብ ወደ ላባ ቤት መድረሱ
1ያዕቆብ ጒዞውን ቀጥሎ በስተምሥራቅ ወዳለው አገር ደረሰ፤ 2እዚያም በሜዳ ላይ አንድ የውሃ ጒድጓድ አየ፤ በሦስት የተከፈሉ የበግ መንጋዎች በጒድጓዱ ዙሪያ ነበሩ፤ መንጋዎቹ ውሃ የሚጠጡት ከዚሁ ጒድጓድ ነበር፤ ጒድጓዱም የሚዘጋበት ድንጋይ ትልቅ ነበር፤ 3መንጋዎቹ ሁሉ እዚያ ከተሰበሰቡ በኋላ እረኞቹ ድንጋዩን አንከባለው ከጒድጓዱ ውሃ ያጠጡአቸው ነበር፤ መንጋዎቻቸውን ካጠጡ በኋላ ግን ድንጋዩን መልሰው በጒድጓዱ አፍ ላይ ይከድኑታል።
4ያዕቆብም እረኞቹን “ወዳጆቼ ሆይ፥ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው።
እነርሱም “እኛ የመጣነው ከካራን ነው” አሉት።
5እርሱም “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁን?” ብሎ ጠየቃቸው።
እነርሱም “አዎ፥ እናውቀዋለን” አሉት።
6እርሱም “ለመሆኑ እርሱ ደኅና ነውን?” አላቸው።
እነርሱም “አዎ፥ ደኅና ነው፤ እንዲያውም ልጁ ራሔል ያቺውልህ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ነች” አሉት።
7ያዕቆብም “ጊዜው ገና ቀን ነው፤ መንጋዎቻችሁንም ወደ ቤት የምታስገቡበት ሰዓት ገና አልደረሰም፤ ታዲያ ለምን ውሃ አጠጥታችሁ አታሰማሩአቸውም?” አለ።
8እነርሱም “እረኞች ሁሉ መንጋዎቻቸውን ይዘው እዚህ ከመሰብሰባቸው በፊት ምንም ማድረግ አንችልም፤ ሁሉም እዚህ ከመጡ በኋላ ግን ድንጋዩን በኅብረት አንከባለን በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉት።
9ያዕቆብም ከእረኞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ ራሔል የአባትዋን በጎች ይዛ ወደዚያ መጣች፤ እርስዋ የበጎች እረኛ ነበረች። 10ያዕቆብ ያጐቱን የላባን በጎች እየነዳች ስትመጣ ራሔልን አይቶ ወደ ጒድጓዱ ሄደ፤ ጒድጓዱ የተከደነበትንም ድንጋይ አንከባሎ በጎቹን አጠጣቸው። 11ከዚህ በኋላ ራሔልን ሳማት፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ አለቀሰ፤ 12“እኔ የአባትሽ እኅት የርብቃ ልጅ ነኝ” አላት። እርስዋም ለአባቷ ልትነግር ሮጣ ሄደች። 13ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን በሰማ ጊዜ ሊቀበለው ፈጥኖ ሄደ፤ ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ ወደ ቤት አመጣው፤ ያዕቆብ የሆነውን ሁሉ ለላባ ነገረው፤ 14ላባም “በእርግጥ አንተ ቅርብ የሥጋ ዘመዴ ነህ” አለው፤ ያዕቆብም አንድ ወር ያኽል ከአጐቱ ጋር ተቀመጠ።
ያዕቆብ ስለ ራሔልና ስለ ልያ ላባን ማገልገሉ
15ላባ ያዕቆብን “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለኝ አይገባህም፤ ስለዚህ ምን ያኽል ደመወዝ ላስብልህ?” አለው። 16ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ታላቂቱ ልያ፤ ታናሽቱ ራሔል ይባሉ ነበር። 17ልያ ዐይነ ልም ስትሆን፥ ራሔል ግን ቁመናዋ የሚያምር የደስ ደስ ያላት ነበረች።
18ያዕቆብ ራሔልን እጅግ ስለ ወደዳት “ራሔልን ብትድርልኝ ሰባት ዓመት አገለግልሃለሁ” አለ።
19ላባም “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጥህ ይሻለኛል፤ እሺ ተስማምቼአለሁ፤ እዚሁ ከእኔ ጋር ኑር” አለው። 20ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ሰባት ዓመት አገለገለ፤ ይሁን እንጂ ራሔልን በጣም ይወዳት ስለ ነበር የቈየበት ጊዜ ጥቂት ቀን ብቻ መስሎ ታየው።
21ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ላባን “እነሆ፥ የአገልግሎት ዘመኔ ተፈጽሞአል፤ ሚስት እንድትሆነኝ ልጅህን ስጠኝ” አለው። 22ላባም የሠርግ ድግስ አዘጋጅቶ በአቅራቢያው የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ ጠራ። 23ነገር ግን በመሸ ጊዜ ላባ በራሔል ምትክ ልያን ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም ወደ ልያ ገባ። 24ላባ ሴት አገልጋዩን ዚልፋን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለልያ ሰጣት። 25በማግስቱ ጠዋት ያዕቆብ አብራው ያደረችው ልያ መሆንዋን ባወቀ ጊዜ ወደ ላባ ሄዶ “ይህ ያደረግህብኝ ነገር ምንድን ነው? ያገለገልኩህ ራሔልን ለማግኘት አልነበረምን? ታዲያ ለምን አታለልከኝ?” አለው።
26ላባም “ታላቂቱ ሳትዳር፥ ታናሺቱን መዳር የአገራችን ልማድ አይደለም፤ 27የልያ ሠርግ ሰባት ቀን እስኪሞላው ድረስ ጠብቅ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰባት ዓመት የምታገለግለኝ ከሆነ ራሔልን እሰጥሃለሁ” አለው።
28ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋር ሰባት ቀን ተሞሽሮ ከቈየ በኋላ፥ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት። 29ላባ ሴት አገልጋዩን ባላን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለራሔል ሰጣት። 30ያዕቆብ ወደ ራሔልም ገባ፤ ከልያም አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያ በኋላ ላባን ሰባት ዓመት አገለገለው።
ለያዕቆብ የተወለዱ ልጆች
31ልያ የራሔልን ያኽል እንዳልተወደደች እግዚአብሔር ባየ ጊዜ ልጅ መውለድ እንድትችል ማሕፀንዋን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መኻን ሆነች፤ 32ልያ ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “እግዚአብሔር መከራዬን ተመለከተ፤ ከእንግዲህስ ወዲያ ባሌ ይወደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል አለችው። #29፥32 ሮቤል፦ በዕብራይስጥ “ረአቡን” ሲሆን “እሰይ ወንድ ልጅ” ወይም “መከራዬን አየልኝ” ማለት ነው። 33እንደገና ፀነሰችና ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “እግዚአብሔር እንዳልተወደድኩ ሰማ፤ ይህንንም ልጅ ደግሞ ሰጠኝ” ስትል ስሙን ስምዖን አለችው። #29፥33 ስምዖን፦ በዕብራይስጥ “ሰማ” ማለት ነው። 34እንደገና ፀነሰችና ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “እንግዲህ ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድኩለት አሁን ባሌ ከእኔ ጋር በፍቅር ይጠመዳል” ስትል ስሙን ሌዊ አለችው፤ #29፥34 ሌዊ፦ በዕብራይስጥ “ይጠመዳል” ማለት ነው። 35እንደገና ፀነሰችና ወንድ ልጅ ወለደች፤ “አሁንስ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ስትል ስሙን ይሁዳ አለችው፤ ከዚህ በኋላ መውለድ አቋረጠች። #29፥35 ይሁዳ፥ በዕብራይስጥ “ምስጋና” ማለት ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 29: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997