የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 43

43
የዮሴፍ ወንድሞች ብንያምን ይዘው እንደገና ወደ ግብጽ መሄዳቸው
1በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ እየበረታ ሄደ፤ 2የያዕቆብ ቤተሰብ ከግብጽ የመጣውን እህል ተመግበው በጨረሱ ጊዜ አባታቸው “እንደገና ወደ ግብጽ ሂዱና ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው።
3ይሁዳ ግን ለአባቱ እንዲህ ብሎ መለሰለት፥ “ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ እፊቴ እንዳትቀርቡ’ በማለት በብርቱ አስጠንቅቆናል፤ 4ስለዚህ ወንድማችንን ይዘን እንድንሄድ ከፈቀድክልን ሄደን እህል እንሸምትልሃለን። 5ይህን የማትፈቅድልን ከሆነ ግን ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ እፊቴ እንዳትቀርቡ’ ስላለን ወደዚያ አንሄድም።”
6ያዕቆብም “ ‘ሌላ ወንድም አለን’ ብላችሁ ለሰውየው በመናገር ለምን ይህን ያህል መከራ አመጣችሁብኝ?” አለ።
7እነርሱም “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተሰባችን አጥብቆ መረመረን፤ ‘አባታችሁ በሕይወት አለን? ሌላስ ወንድም አላችሁን?’ ብሎ ጠየቀን፤ እኛም ለጥያቄው ተገቢውን መልስ ሰጠን፤ ስለዚህ ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ እንድትመጡ’ እንደሚለን እንዴት ልናውቅ እንችል ነበር?”
8ይሁዳም አባቱን እንዲህ አለ፤ “ልጁን በእኔ ኀላፊነት አብሮን እንዲሄድ አድርግ፥ ሳንዘገይ አሁኑኑ ጒዞ እንጀምር፤ ይህ ከሆነ፥ እኛም አንተም ልጆቻችንም ሁሉ በራብ ከመሞት እንድናለን። 9ልጁን በእኔ ዋስትና ስጠኝ፤ ስለ እርሱ እኔ ተጠያቂ እሆናለሁ፤ በደኅና ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው በሕይወቴ ዘመን ተወቃሽ ልሁን። 10ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ እስከ አሁን ሁለት ጊዜ እዚያ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።”
11አባታቸው ያዕቆብም እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ መሄዳችሁ የማይቀር ከሆነ ለአገረ ገዢው ገጸ በረከት የሚሆን ምድራችን ከምታፈራው ምርጥ ነገር ሁሉ በስልቻዎቻችሁ ጨምራችሁ ሂዱ፤ ይኸውም በለሳን፥ ማር፥ ቅመማ ቅመም፥ ከርቤ፥ ተምርና ለውዝ ይዛችሁ ሂዱ። 12ከዚህ በፊት በየስልቻዎቻችሁ ጫፍ ተመልሶ የነበረው ገንዘብ በስሕተት ሊሆን ስለሚችል እጥፍ ገንዘብ ይዛችሁ ሂዱ። 13ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደ ሰውየው በቶሎ ሂዱ። 14ብንያምንና ሌላውንም ወንድማችሁን መልሶ እንዲሰጣችሁ ሁሉን የሚችል አምላክ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እኔ በበኩሌ ልጆቼን ካጣሁ፥ ባዶ እጄን መቅረቴ ነው።”
15ስለዚህ ወንድማማቾቹ ገጸ በረከቱንና እጥፍ ገንዘብ ይዘው ከብንያም ጋር ወደ ግብጽ ለመሄድ ጒዞ ጀመሩ፤ እዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ ዮሴፍ ፊት ቀረቡ። 16ዮሴፍ ብንያምን ከእነርሱ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ ጠራውና “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ውሰዳቸው፤ ዛሬ ቀን ከእኔ ጋር ምሳ ስለሚበሉ አንድ ከብት ዕረድና አዘጋጅ” አለው።
17አዛዡም ዮሴፍ በነገረው መሠረት ሰዎቹን ወስዶ ወደ ቤት አስገባቸው። 18“ወደ እዚህ ያመጡን በመጀመሪያ ጊዜ በስልቻዎቻችን ውስጥ ተመልሶ ስለ ተገኘው ገንዘብ ሳይሆን አይቀርም” በማለት፤ ሰዎቹ ወደ ዮሴፍ ቤት በሚሄዱበት ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ “በዚህ ምክንያት ያሠቃዩናል፤ አህዮቻችንን ወስደው እኛንም የእነርሱ ባሪያዎች ያደርጉናል” ብለውም አሰቡ።
19ስለዚህ ወደ ቤቱ በር አጠገብ ሲደርሱ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አሉት፤ 20“ጌታዬ ከዚህ በፊት እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤ 21ስንመለስ በመንገድ ለዐዳር በሰፈርንበት ቦታ ስልቻዎቻችንን ስንፈታ የያንዳንዳችንን ገንዘብ ምንም ሳይጐድልለት በየስልቻዎቻችን አፍ ላይ ተቋጥሮ አገኘነው። እነሆ፥ ያንን ገንዘብ መልሰን አምጥተናል። 22አሁን እህል የምንሸምትበትንም ገንዘብ በተጨማሪ ይዘናል፤ በዚያን ጊዜ ገንዘባችንን መልሶ በየስልቻዎቻችን ማን እንደ ከተተው አናውቅም።”
23የቤቱም አዛዥ “በዚህ ጉዳይ ጭንቀትና ፍርሀት አይድረስባችሁ፤ የእናንተና የአባታችሁ አምላክ ይህን ገንዘብ በየስልቻዎቻችሁ አስቀምጦላችሁ ይሆናል፤ የእናንተን ገንዘብ ግን እኔ ተቀብዬአለሁ” አላቸው። ከዚህ በኋላ ስምዖንን ወደ እነርሱ አመጣው።
24የቤቱ አዛዥ ወንድማማቾቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸውና እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ ሰጣቸው፤ ለአህዮቻቸውም ገፈራ ሰጣቸው። 25ከዮሴፍ ጋር ምሳ እንደሚበሉ ተነግሮአቸው ስለ ነበር፥ ዮሴፍ በምሳ ሰዓት እስከሚመጣ ድረስ ለእርሱ የሚያቀርቡለትን ስጦታ አዘጋጁ።
26ዮሴፍ ወደ ቤት በገባ ጊዜ፥ እርሱ ወዳለበት ክፍል ገብተው ያመጡትን ስጦታ አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት። 27እርሱም ስለ ደኅንነታቸው ከጠየቃቸው በኋላ “ያ የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ እንዴት ነው? አሁንም በሕይወት አለን?” አላቸው።
28እነርሱም “አገልጋይህ አባታችን በሕይወት አለ፤ ጤንነቱም የተሟላ ነው” አሉት። ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት።
29ዮሴፍ የእናቱ ልጅ የሆነውን ወንድሙን ብንያምን ባየው ጊዜ “ ‘ታናሽ ወንድም አለን’ ብላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ይህ እርሱ ነውን?” አለና “ልጄ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለው። 30ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ ስለ ተነካ ከዚያ ተነሥቶ ሄደ፤ ወደ እልፍኙም ገብቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
31ፊቱንም ከታጠበ በኋላ ወጣ፤ ራሱንም በመቈጣጠር ምሳ እንዲቀርብ አዘዘ።
32ግብጻውያን ከዕብራውያን ጋር አብሮ መመገብን እንደ ጸያፍ ይቈጥሩት ስለ ነበር ለዮሴፍ ብቻውን አንድ ገበታ፥ ለወንድማማቾቹ ሌላ ገበታ፥ እዚያ ይመገቡ ለነበሩ ግብጻውያንም ሌላ ገበታ ተዘጋጀ፤ 33ወንድማማቾቹ ከታላቁ አንሥቶ እስከ ታናሹ በዕድሜ ተራ በዮሴፍ ፊት ለፊት ተቀመጡ፤ እንዴት እንደ ተቀመጡ ባዩ ጊዜ በመደነቅ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 34ለዮሴፍ ከቀረበለት ምግብ እየተወሰደ ይሰጣቸው ነበር፤ ለብንያም ግን ከሌሎቹ አምስት እጥፍ ተሰጠው፤ በዚህ ዐይነት ከዮሴፍ ጋር እስኪጠግቡ በልተው ጠጥተው ተደሰቱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ