ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 1
1
እግዚአብሔር በልጁ አማካይነት እንደ ተናገረ
1እግዚአብሔር በቀድሞ ዘመናት በተለያዩ መንገዶች፥ በነቢያት አማካይነት ለአባቶቻችን ብዙ ጊዜ ተናግሮ ነበር፤ 2አሁን ግን በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ሁሉን ነገር ወራሽ ባደረገው በልጁ አማካይነት ለእኛ ተናገረን፤ ዓለምንም ሁሉ የፈጠረው በእርሱ ነው። 3እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ነው፤ እርሱ በባሕርዩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ትክክል ነው። በኀያል ቃሉ ዓለምን ሁሉ ደግፎ ይዞአል፤ ሰዎችንም ከኃጢአት ካነጻ በኋላ በሰማይ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል።
እግዚአብሔር ወልድ ከመላእክት እጅግ የላቀ መሆኑ
4ለእርሱ የተሰጠው ስም ከመላእክት ስም በላይ እንደ መሆኑ መጠን የእግዚአብሔር ልጅ ከመላእክት እጅግ በጣም የላቀ ነው። #መዝ. 2፥7፤ 2ሳሙ. 7፥14፤ 1ዜ.መ. 17፥13።
5እግዚአብሔር ከቶ ከመላእክት መካከል፥
“አንተ ልጄ ነህ፤ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤”
ወይም
“እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል”
ያለው ማንን ነው?
6እግዚአብሔር የበኲር ልጁን ወደ ዓለም በላከ ጊዜ
“የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል። #ዘዳ. 32፥43።
7ስለ መላእክቱ ግን
“መላእክቱን መናፍስት፥
አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል። #መዝ. 104፥4።
8ስለ ልጁ ግን፥
“አምላክ ሆይ! ዙፋንህ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይኖራል፤
መንግሥትህንም በትክክል ታስተዳድራለህ፤
9ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ፤
በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አምላክህ መረጠህ፤
ከጓደኞችህም ይበልጥ ደስታን በሚሰጥ ቅባት ቀባህ” ይላል። #መዝ. 45፥6-7።
10እንዲሁም፥
“ጌታ ሆይ! አንተ በመጀመሪያ ምድርን መሠረትህ፤
ሰማያት የእጅህ ሥራ ናቸው፤
11እነርሱ ሁሉ ይጠፋሉ፤
አንተ ግን ትኖራለህ፤
እነርሱ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃሉ።
12እንደ መጐናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ፤
እነርሱም እንደ ልብስ ይለወጣሉ።
አንተ ግን ሁልጊዜ ያው ነህ፤
ለዘመንህም ፍጻሜ የለውም” ይላል። #መዝ. 102፥25-27።
13እግዚአብሔር ከመላእክቱ መካከል፥
“ጠላቶችህን ከሥልጣንህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ
በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ማንን ነው? #መዝ. 110፥1።
14ታዲያ፥ መላእክት ሁሉ የሚድኑትን ሰዎች ለማገልገል የሚላኩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉምን?
Currently Selected:
ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997